በተከታታይ የወንጀል ክስ አሰማም ሂደት ዙሪያ በተዘጋጀ ጥናት ላይ የማረጋገጫ እና የውይይት መድረክ (Validation and Consultation Workshop) ተካሔደ
/ Categories: News

በተከታታይ የወንጀል ክስ አሰማም ሂደት ዙሪያ በተዘጋጀ ጥናት ላይ የማረጋገጫ እና የውይይት መድረክ (Validation and Consultation Workshop) ተካሔደ

ከፌደራል ፍርድ ቤቶች፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እና ከፌደራል ጠበቆች ማሕበር የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች፣ ዳኞች እንዲሁም ባለሙያዎች የተሳተፉበትና በተከታታይ የወንጀል ክስ አሰማም ሂደት (Continuous Criminal Trial) ላይ ‹‹Assessment of gaps that obstruct continuous ctriminal trials in federal courts›› በሚል ርዕስ በተከናወነ ጥናት ላይ የማረጋገጫ እና የምክክር መድረክ (Validation Workshop) ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ተካሄዷል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ ዳኛ አበበ ሰለሞን በመድረኩ መክፈቻ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚከናወኑ የለውጥ ሥራዎች መካከል በወንጀል ፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገኝበት እና በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን ለመለየት የሚስያስችሉ የተለያዩ ጥናቶችን ማካሄድ እና የጥናቶችን ግኝት መሠረት ያደረገ መፍትሄ መስጠት የማሻሻያ ስራው አካል መሆኑን ጠቁመው ይህ ጥናት በፍትሐዊነት የመዳኘት መብትን ከማረጋገጥ እና የተፋጠነ ፍትህን ከማስፈን አንፃር የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

ጥናቱን ያዘጋጁት የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ በሆኑት አቶ ደሳ ቡልቻ ተከታታይ የወንጀል ክስ አሰማም ሂደት ዓላማ የወንጀል ክስ ሒደት ከተጀመረ በኋላ ሳይቆራረጥ እንዲጠናቀቅ ማድረግ መሆኑን እና የክስ መስማት ሒደቱ በቀጠሮ መሻገር ካለበትም በበቂ ምክንያት እና ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ እንዲከናወን ለማስቻል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ተከታታይ የወንጀል ክስ አሰማም ጠቀሜታም የጉዳዮችን መዘግየት ለማስቀረት፤ በፍትሐዊነት የመዳኘት መብትን ለማረጋገጥ እና በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑን በመግለፅ የተለያዩ አገራት ተሞክሮዎችንም አንስተዋል፡፡

በአገራችን እስካሁን እየተሰራበት ባለው የወንጀል ሥነሥርዓት ሕግ ተከታታይ የወንጀል ክስ አሰማምን የተመለከተ በግልጽ የተቀመጠ ድንጋጌ ባለመኖሩና የወንጀል ክስ አሰማምን የተመለከቱ የተወሰኑ ድንጋጌዎች አከራካሪ በመሆናቸው በአገራችን ፍርድ ቤቶች የወንጀል ክስ አሰማም በተቆራረጠና በተበጣጠሰ ሁኔታ እንዲካሄድ እና ይህም ለጉዳዮች መዘግየት ምክንያት እንደሆነ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

አሁን በረቂቅ ደረጃ ላይ በሚገኘው የወንጀል ሥነሥርዓት ሕግ ተከታታይ የሆነ የወንጀል ክስ አሰማም (Continuous Criminal Trial) ለሁሉም የወንጀል ሕጎች ላይ ተግባራዊ እንዲሆን የተደነገገ መሆኑን በመጠቆም ለተግባራዊነቱም ፍርድ ቤቶች እና በዳኝነት ስርዓቱ ባለድርሻ የሆኑ አካላት በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ከማሳደግ ጀምሮ ተከታታይ የወንጀል ክስ አሰማም ሂደትን ለመተግበር የሚያስችል ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተብራርቷል፡፡

የጥናት ውጤቱ ከቀረበ በኋላ የመድረኩ ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት ተከታታይ የሆነ የወንጀል ክስ አሰማም (Continuous Criminal Trial) ተግባራዊ መሆኑ ተገቢነት ያለው መሆኑን ገልጸው በአፈጻጸም ረገድ ሊያጋጥሙ በሚችሉ ተግዳሮቶች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን አቅርበው ከጥናቱ አቅራቢ ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠባቸው ሲሆን በቀጣይ ከመድረኩ የተገኙ ግብዓቶችን በመውሰድ የጥናቱን አላማ ለማሳካት የሚያስችል ሰነድ እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል፡፡

ጥናቱ የተዘጋጀው በአውሮፓ ሕብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ፍትህ ስርአት ማሻሻያ ፕሮግራም ነው፡፡

Previous Article ፍርድ ቤቱ የሰበር ዉሳኔ የድምጽ ቅጂ ለኢትዮጵያ ዓይነ ስዉራን ብሔራዊ ማህበር አበረከተ
Next Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዋይድ ኤርያ ኔትወርክ ፕሮጀክት አፈጻጸም ያለበት ደረጃ ክትትልና ግምገማ ተካሄደ
Print
5080