Friday, November 7, 2025 / Categories: News በአስማሚነት ክህሎት ዙሪያ ሲሰጥ የነበረዉ የተግባር ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት ከጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 27 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ 4 ቀናት በተግባር ሲሰጥ የነበረዉ የአስማሚነት ክህሎት ስልጠና ተጠናቋል፡፡ በስልጠናዉ መድረክ ከተሰጠዉ አለምአቀፋዊ የአስማሚት መርሆዎች፣ ስትራቴጂዎች እና ስልቶች የሚያብራራ ገለጻ በተጨማሪ በሰልጣኞች በተከወኑ እነዚህኑ መርሆች መሰረት ያደረጉ የተግባር ልምምዶች በአተገባበር ረገድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት ሰፊ እና ዘርፈ ብዙ ውይይት ለማድረግ ተችሏል፡፡ ስልጠናዉን የሰጡት አቶ ቴዎፍሎስ ኢክፓን የቅድመ ማስማማት ስልቶችና የማስማማት ክህሎቶች፣ የአስማሚዎች ሚና፣ ከስምምነት በኋላ ስለሚዘጋጁ ዉሎች እና ይዘታቸውን በተመለከተ ያላቸዉን በተግባር የዳበረ ልምድ ለሰልጣኞች አጋርተዋል፡፡ በስልጠናዉ ማጠቃለያ መርሀ-ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ፉዓድ ኪያር የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የለዉጥ ስራ ዋነኛ አካል የሆነዉን የፍርድ ቤት መር አስማሚነት /court annexed mediation/ የሚተገበረው በተከራካሪዎች መካከል ያለዉን ቀጣይ ግንኙነት ጤናማ ማድረግንና ዉዝፍ መዛግብትን በመቀነስ ፍርድ ቤቶች ከተለመደዉ አሰራር ወጥተዉ ዘመናዊ በሆነ መንገድ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን መቀየርን ዓላማ በማድረግ መሆኑን አስታውሰው፤ በፍርድ ቤቶች እና ከፍርድ ቤቱ ዉጪ ባለዉ ማህበረሰብ ዘንድ ስለማስማማት ያለዉን ዝቅተኛ አመለካከት በማሻሻል ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት በትጋትና በቁርጠኝነት በጋራ መስራት ተገቢ በመሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ስልጠናውን በማዘጋጀቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር የሆኑት ክብርት ዳኛ ህውስት አሸናፊ ስልጠናውን በማዘጋጀት ሂደት የገንዘብ ድጋፍ ያደረገውን UNFPAን አመስግነው በቀጣይም የስራ ክፍሉ በፍትህ ስርአቱ ውስጥ ለሚገኙ ባለሞያዎች መሰል የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን የሚያዘጋጅ መሆኑን ጠቅሰው የዳኝነት ስርአቱን ለህጻናት ተስማሚ እና ምቹ በማድረግ ሂደት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ለማከናወን በእቅድ መያዙን እና ትግበራውም ግቡን እንዲመታ አጥብቀው እንደሚሰሩ ለስልጠናው ተሳታፊዎች አስገንዝበዋል፡፡ Previous Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የሶማሊ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቴክኖሎጂ ስራዎችን በይፋ አስጀመሩ Next Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሪሶርስ ኢንሪቺንግ አፍሪካን ላይቭስ በሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት አስተባባሪነት የተሰበሰቡ መጽሃፍቶችን ተረከበ Print 453