በአገልግሎት አሰጣጥና የተገልጋዩች አያያዝ ላይ ስልጠና ተሰጠ
/ Categories: News

በአገልግሎት አሰጣጥና የተገልጋዩች አያያዝ ላይ ስልጠና ተሰጠ

ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰው ሃብት ስራ አመራር ዳይሬክተሮች፣ ቡድን መሪዎች፣ በሬጅስትራር ስር ላሉ እና ለሌሎች የአስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞች ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም በአገልግሎት አሰጣጥና የተገልጋዩች አያያዝ ላይ ስልጠና ተሰጥቷል ፡፡

ስልጠናውን ያስጀመሩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ድሪባ ፈዬራ ሲሆኑ በአንድ ተቋም የሚያገለግል ሰራተኛ ተቋሙን በሚያገለግልበት ወቅት ሊያውቃቸው ከሚገቡት መሰረታዊ ጉዳይ የተቋሙን ራዕይ በሚገባ ማወቅ እና መዳረሻውን መረዳት መሆኑን ገልጸው ራዕይን ከማሳካት አኳያ እያንዳንዱ ሠራተኛ ድርሻዉ ምን እንደሆነ በሚገባ መረዳት እንዳለበት እና የፍርድ ቤቶችን ልዩ ባህርይም በአግባቡ ተረድቶ ማገልገል እንደሚገባዉ ገልጸዋል፡፡

ስልጠናዉም ሰልጣኞች በዚህ መሰረታዊ ጉዳይ ላይ ግንዛቤ አግኝተዉ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር የድርሻቸውን እንዲወጡ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ስልጠናውን የሰጡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰው ሃብት ስራ አመራር ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አስራት ደቻሳ ሲሆኑ የስልጠናውን ዓላማ አገልግሎት አሰጣጥና የተገልጋዮች አያያዝ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን ገልጸው በአገልግሎት አሰጣጥ መከተል ስለሚገባቸው እሴቶች፣ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ መርሆች፣ የተግባቦት መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳቦች በሚሉ እና ሌሎች ነጥቦች ላይ በሰፊው ገለጻ አድርገዋል ፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ነሞ አዱኛ ሰልጣኞች መሰረታዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ክህሎቶችን ማለትም ተገልጋይን ማድመጥ፣ መልካም በሆነ ተግባቦት ማገልገል፣ ትዕግስትን መላበስ፣ ችግር ፈች መሆን፣ በቡድን መስራት፣ የሚሰጠውን አገልግሎት በሚገባ ማወቅ፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እና የሚሰራውን ስራ ውጤት በመከታተል ትኩረት ሰጥተው እንዲያገለግሉና የስራቸው መርህ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

Previous Article በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በወንጀል ችሎት በሚታዩ ችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ በተደረገ ጥናት የግብዓት ማሰብሰቢያ ዉይይት ተደረገ
Next Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢኮርት ትግበራ ላይ ለፍትህ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ገለጻ ተደረገ
Print
287