በኢፋይሊንግ፣ ኢሊቲጌሽን እና ኤሌክትሮኒክ ሪከርድ አመራር አፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ ላይ የውይይት መድረክ ተካሄደ
/ Categories: News

በኢፋይሊንግ፣ ኢሊቲጌሽን እና ኤሌክትሮኒክ ሪከርድ አመራር አፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ ላይ የውይይት መድረክ ተካሄደ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በፌደራል ፍርድ ቤቶች የኢፋይሊንግ፣ ኢሊቲጌሽን እና ኤሌክትሮኒክ ሪከርድ አመራር የአፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ ላይ ከፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ ሃላፊዎችና ተጠሪ ዳኞች፣ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ከፌደራል ማረሚያ ቤት፣ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከፌደራል ጠበቆች ማህበር፣ ከህግ ባለሙያዎች ማህበር እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በቀን 19/04/2017 ዓ.ም የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በፌደራል ፍርድ ቤቶች በርካታ የዲጂታላይዜሽን ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አውስተው መመሪያው ዳኞች፣ የዳኝነት አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው ተገልጋይ፣ ጠበቆች፣ እንዲሁም የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ወደ ዲጂታላይዜሽን ስርአት ለማምጣት የህግ ማዕቀፍ በመሆን የሚረዳ እንዲሁም ቴክኖሎጂዎቹ አላማ ያደረጉትን የፍትህ ተደራሽነትና ግልጸኝነትን ለማሳካት የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለውም ፍርድ ቤቶችን ወደ ዲጂታላይዜሽን ስርዓት ለማምጣት በተሰራው ስራ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ በርካታ መዝገቦችን ወደ ኤሌክትሮኒክስ ፋይል መቀየር የተቻለ መሆኑንና በፌደራል ከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ደረጃም ስራዎቹ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው ሁሉም የፍርድ ቤት ሰነዶችን በኤሌክትሮኒክ ፎርም ለመቀየር እቅድ መያዙንም ተናግረዋል፡፡  

ረቂቅ መመሪያውን የማዘጋጀት ሂደት በበላይነት የሚያስተባብሩት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር ዳኛ አበበ ሰለሞን መመሪያውን ማውጣት ያስፈለገበት ምክንያት እና መመሪያው ያካተታቸውን ድንጋጌዎች አስመልክቶ ገለፃ አድርገዋል::

የኤሌክትሮኒክ አቤቱታ አቀራረብ ባለጉዳዮች ጉዳያቸውን በወረቀት በማባዛት የሚያወጡትን ወጪ እና የመዝግብ መጥፋት፣ መጉደልና ሌሎች የደህንነት ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ለዳኞች ሰነዶችን በፍጥንት ተመልክተው ትዕዛዝ/ውሳኔ እንዲሰጡ የሚረዳ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሬጅስትራሮች፣ የሚመለከታቸው የፍርድ ቤቱ ሰራተኞች እንዲሁም ጠበቆች ጉዳዮችን በቀላሉ እንዲከታተሉ፣ እንዲፈጽሙና እንዲያስፈጽሙ የሚረዳ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በረቂቅ መመሪያው ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ከየተቋሙ ተሳታፊዎች በርካታ ግብዓት ተሰብስቧል፡፡

የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝንፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ክቡር ፓስተር ዳንኤል ጀስቲስ ፎር ኦል ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በርካታ ፕሮጀክቶችን መስራታቸውን አውስተው አሁን ላይ ከምንግዜውም በተሻለ አብሮ የመስራት እድሎች ያሉ በመሆኑ ይህን እድል በመጠቀም ክፍተቶችን በጋራ እየሞሉ መልካም የሪፎርም ተግባራትን የማጠናከር ስራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ባደረጉት ንግግር ረቂቅ መመሪያው እንዲዘጋጅ ላደረጉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች እና መመሪያውን በማዘጋጀት ለተሳተፉት እንዲሁም መድረኩ እንዲዘጋጅ ድጋፍ ላደረገው ጀስቲስ ፎር ኦል ፒ.ኤፍ ኢትዮጵያ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Previous Article ዓለም አቀፍ የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከበረ
Next Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህንጻ ግንባታ ማስጀመሪያ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ
Print
952