Monday, March 3, 2025 / Categories: News በከባድና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ የተዘጋጀ ሥልጠና ለፌዴራል እና ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ተሰጠ ለፌደራል ፍርድ ቤቶች እና ከሁሉም ክልል ፍርድ ቤቶች ለተውጣጡ ዳኞች እንዲሁም ለወታደራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች በከባድና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ የተዘጋጀ የአንድ ቀን ስልጠና የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሄደ፡፡ ዳኞች በከባድ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ ያላቸውን እውቀት እና ክህሎትን እንዲያሳድጉ ለማስቻል የተዘጋጀውን ሥልጠና በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ሲሆኑ በንግግራቸዉም በአሁኑ ጊዜ የዳኞችን ስልጠና አሰጣጥ ስርዓትን ከማዘመን አንፃር ጥናትን መሰረት በማድረግ ከሚዘጋጁ ሞጁሎች መሆኑን ገልጸዉ በዛሬዉ እለትም የቀረበዉ የስልጠና ሞጁል በዘርፉ የካበተ ልምድ ባላቸዉ አማካሪዎች መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡ ስልጠናው ከባድ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተመለከተ በአጠቃላይ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ እና በህግ አተረጓጎም ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያግዝ እና አተገባበር ላይም አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሲሆን ስልጠናዉ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ የሕግ ምሁራን ማለትም በዶ/ር ታደሰ ስሜ፣ ዶ/ር ደጀኔ ግርማ እንዲሁም በዶ/ር መንበረፀሐይ ታደሰ ተሰጥቷል፡፡ ስልጠናውን ተከትሎ ከተሳታፊዎቹ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው በአሠልጣኞቹ ምላሽና በቂ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ድሪባ ፈዬራ በበኩላቸው አሰልጣኝ ምሁራኖቹን እንዲሁም ተሳታፊ ዳኞችን አመስግነው የስልጠናው ርዕሰ ጉዳይ ሰፊ እንደመሆኑ መጠን በቀጣይ ተመሳሳይ መድረኮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ የስልጠና መድረኩ የተዘጋጀው በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ከአውሮፓ ህብረት የወንጀል ፍትህ ስርዓት ማሻሻያ በተገኘ ድጋፍ ነው፡፡ Previous Article የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የለውጥ ሥራ ተፈጻሚ ለማድረግ የፍርድ ቤቶችን የሰው ኃይል አቅም መገንባት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለጸ Next Article የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ የግብአት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ ተካሔደ Print 858