Monday, September 8, 2025 / Categories: News በኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቆይታ ያደረጉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ልምዳቸውን አካፈሉ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ የተመራ የዳኞች ልዑክ ቡድን "የተቀናጀ የጉዳዮች ማኔጅመንት ሲስተም እና የኤሌክትሮኒክ ሪከርድ ማኔጅመንት"(Integrated Case Management System and Electronic Record Management) ላይ ኬንያ በመገኘት ያገኘውን ልምድ በቀን 02/13/2017 ዓ.ም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች አካፍለዋል፡፡ ልዑክ ቡድኑን የመሩት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ልዑክ ቡድኑ በኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በነበረው ቆይታ ያገኘውን መልካም ተሞክሮዎችን በማንሳት አሁን ላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ተጠቃሽ ከሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ቀሪ የቤት ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ያሉትን መልካም አሰራሮችን ለማሳደግና አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ፣ ይቀራሉ ተብለው በሚታሰቡና በሌሎች ያደጉ ሀገራት ፍርድ ቤቶች ላይ እንደ መልካም ተሞክሮ የሚወሰዱትን ደግሞ ለመተግበር ከምንግዜውም በላይ ፍርድ ቤቶቻችን የተሻለ አቋም ላይ ያሉ በመሆኑ የሚመጡትን ፈተናዎችን ለመቋቋምና የመፍትሄ ሀሳቦችን ለማመንጨት ተነሳሽነት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች አሁን ላይ ከቴክኖሎጂ አንጻር የላቀ አፈጻጸም ላይ የደረሱ መሆኑን አንስተው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም እንደ ግብ የያዘው ኢ-ኮርት ኢትዮጵያ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ፍርድ ቤቶች በሙሉ እንዲተገበር ታሳቢ በማድረግ የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት እና በፍርድ ቤቶች ታሪክ ከፍተኛ የሆነ በጀት ተመድቦለት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም እየለሙ ያሉት የቴክኖሎጂ መሰረት ልማቶቹ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉት የተቋም ዝግጁነትና የባለድርሻ አካላት ሚና እያደገ ሲሄድ በመሆኑ አመራሮች፣ ዳኞችና የፍርድ ቤት ማህበረሰብ በመመስከር ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂዎቹ ወደ ትግበራ እንዲገቡ የስራው ባለቤት በመሆን ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመቋቋምና ክፍተቶችን እየሞሉ መሄድ የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ በመምከር እንዲሁም ለስራው መሳካት ከፍተኛ ጥረትና ትጋት በማድረግ የታሪኩ አካል ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ Previous Article ወጥነትና ተገማችነት በሌላቸው የሰበር ውሳኔዎች እና የወደፊት አቅጣጫ ላይ የውይይት መድረክ ተካሄደ Next Article በሶማሌ ክልል መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አሊ ባሩድ የተመራ ልዑክ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የልምድ ልውውጥ አደረገ Print 374