Monday, June 23, 2025 / Categories: News, CJPO NEWS በወንጀል ነክ ድርጊት ዉስጥ ገብተዉ ከተገኙ ህጻናት እንዲሁም በሴቶች እና ህጻናት ችሎት ለሚሰሩ የፌዴራል ዳኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት በወንጀል ነክ ድርጊት ዉስጥ ገብተዉ ከተገኙ ህጻናት እንዲሁም በሴቶች እና ህጻናት ችሎት ለሚሰሩ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰኔ 14 እና 15 ቀን 2017 ዓ.ም ተሰጥቷል፡፡ በስልጠናዉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዳኛ ተክለኃይማኖት ዳኜ በፍትህ ስርዓቱ የሚያልፉ ህፃናት ደህንነትና ጥቅም ከማስከበር አንጻር ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ እና ይህ ስልጠናም የዚሁ አካል እንደሆነ ገልጸዉ በቀጣይ ባሉት ጊዜያት አገልግሎት አሰጣጡን በአይነትና በጥራት በማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የቀድሞዉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት በአሁኑ በኢትዬጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ አባል ክቡር አቶ ተኽሊት ይመሰል ህጻናት በወንጀል ነክ ድርጊት ዉስጥ ገብተዉ ሲገኙ የእርምት እርምጃ አወሳሰንና አተገባበር በአለም አቀፍና በኢትዮጵያ ህጎች እይታ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ህፃናት በወንጀል ነክ ድርጊት ዉስጥ ገብተዉ ሲገኙ ሊወሰዱ ስለሚገቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እና ወንጀል ፈፅመዉ የተገኙ ህፃናት ደህንነታቸዉ ተጠብቆ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር ምን መምሰል እንዳለበትም ህጉን በማጣቀስ አብራርተዋል፡፡ በመቀጠልም በሴቶችና ህፃናት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች በምርመራ፣ክስ በማሰማት እና በፍርድ ሂደት ዉስጥ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችና መፍትሔዎች ላይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክቡር ዳኛ አቶ አለማየሁ ዳባ ዘርዘር ያለ ገለጻ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የህፃናት መብት አስመልክቶ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስገዳጅ የህገ- መንግስት ትርጉም የተሰጠባቸዉ ዉሳኔዎች በመዳሰስ በህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ ፅ/ቤት የህገ-መንግስት ትርጉም ጉዳዮች ዳይሬክተር በአቶ ያደታ ግዛዉ ቀርቧል፡፡ በገለፃዎቹ ላይ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ሃሳብ ጥያቄዎች ሰፊ ዉይይት ከተደረገባቸዉ በኃላ ስልጠናዉን በሰጡት አሰልጣኞች ማብራሪያ እና ምላሽ የተሰጠባቸዉ ሲሆን ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬቱ በወንጀል ጉዳይ ዉስጥ የገቡ ህፃናት የጥንቃቄ እርምጃዎች ወጥ፣ ተገማች እንዲሁም የህጻናትን መብት እና ጥቅም ያደረጉ እንዲሆኑ ዕቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮሚዩኒኬሽንና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክቶሬት Previous Article የኢ-ፋይሊንግ እና የፕላዝማ ችሎት የስራ ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ Next Article የፌደራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት አዋጅ ማሻሻያ እና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሄደ Print 768