በዳኝነት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከተለመደው አሠራር ወጣ ያሉ አዳዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዲሱ አመራር በፍ/ቤቱ ሥራ የጀመረው የነበረውን አሠራር ለማስቀጠል ብቻ ሳይሆን በዳኝነት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከተለመደው አሠራር ወጣ ያሉ አዳዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ መሆኑን የፍ/ቤቱ ፕሬዚደንት ሆነው የተሾሙት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ገለጹ፡፡
ክቡር ፕሬዚደንቱ ይህን የገለጹት እርሳቸውን ጨምሮ የፍ/ቤቱ ም/ፕሬዚደንት ሆነው አዲስ የተሾሙት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ከፍ/ቤቱ የአስተዳደር ዘርፍ አመራሮችና የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ጋር ለመተዋወቅና በቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ሀሳብ ለመለዋወጥ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም በፍርድ ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ ክቡር ፕሬዚደንቱ ከፍርድ ቤቱ የሥራ ክፍሎች በተለይም ደግሞ ከዳኝነት ሥራው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው የሥራ ሒደቶች ውጤታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የአሰራር ለውጦች ተግባራዊ ሆነው ማየት እንደሚፈልጉም አስምረውበታል፡፡
እነዚህ የአሠራር ለውጦችም በሥራ ክፍሎች ታቅደው የሚከናወኑ ወይም አመራሩ በሚሠጠው አቅጣጫ መሠረት የሚተገበሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ የጠቆሙት ክቡር ፕሬዚደንቱ፣ ከሥራ ክፍሎቹ ኃላፊዎች አሠራራቸውን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ወይም ለአሠራር ማነቆ የሆኑባቸው ጉዳዮች ካሉ በመድረኩ ላይ ውይይት እንዲደረግባቸው በሰጡት አስተያየት መሠረት ከተሰብሳቢዎቹ የተወሰኑ አስተያየቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ክቡር ፕሬዚደንቱ አክለውም የዳኝነት አገልግሎቱን ለማዘመን እና ተገልጋይ ተኮር ለማድረግ በትንንሽ ጉዳዮች ላይ ፈጣን ለውጥ በማምጣት በሒደት በትልልቅ ጉዳዮች ላይም የሚፈለገውን የአሰራር ቅልጥፍና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል አስረድተው፣ የፍርድ ቤቱን አገልግሎት አሠጣጥ ለማዘመን እና ቀልጣፋ ለማድረግ የተያዘውን ትልቁን ግብ እስካሳካ ድረስ ከሥራ ክፍሎች ጋር በጋራ እና ተቀራርበው ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
239