በጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫ ጉዳዮችን እንዲመለከቱ ለተደራጁ ልዩ ችሎቶች የስራ አቅጣጫ ተሰጠ
/ Categories: News

በጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫ ጉዳዮችን እንዲመለከቱ ለተደራጁ ልዩ ችሎቶች የስራ አቅጣጫ ተሰጠ

በጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫ ጉዳዮችን እንዲመለከቱ ለተደራጁ ልዩ ችሎቶች የስራ አቅጣጫ ተሰጠ

 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የሚታዩባቸው ችሎቶች በጠቅላይ ፍ/ቤት መደራጀታቸውን አፈጻጸማቸውን በተመለከተ ለፕሬዝደንት ጽ/ቤትና ለሬጂስትራሮች የስራ አቅጣጫ ሰጡ፡፡ 

 

ክብርት ፕሬዝደንት ወ/ሮ መዓዛ በሰጡት የስራ አቅጣጫ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የሚስተናገዱበት የምርጫ ችሎቶች መደራጀት አስፈላጊ መሆኑን በ “ኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር” አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ተደንግጓል፡፡ በዚሁ መሰረት የምርጫ ችሎት ድልድል ተከናውኗል ብለዋል፡፡

 

የምርጫ ችሎቶቹ ከመደበኛ ችሎቶች በተጓዳኝ የሚካሄዱ ሲሆን የምርጫ መዛግብት ፍሰት እየጨመረ ከመጣ ተጨማሪ ችሎቶች ሊደራጁ ይችላሉ፡፡ በተለይም ምርጫው በሚከናወንበት ግንቦት ወር ወይንም ምርጫው በተከናወነበት ተከታታይ ሳምንታት የምርጫ ጉዳዮች ፍሰት አሁን በተመደቡት ችሎቶች ማስተናገድ አስቸጋሪ የሚሆን ከሆነ የምርጫ ጉዳዮች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲስተናገዱ አስፈላጊ መመሪያዎች ሊተላለፉ እንደሚችሉም ክብርት ፕሬዝደንቷ ገልጸዋል፡፡

 

መጪው ጠቅላላው ሃገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ፍ/ቤት ቁልፍ ሚና ያለው ባለድርሻ አካል መሆኑ ያመለከቱት ክብርት ፕሬዝደንቷ በአዲስ መልክ በጸደቀው የምርጫ ሕግ 1162/2011 ላይ ጠለቅ ያለ ስልጠና ተዘጋጅቶ ለዳኞች መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የምርጫ ጉዳዮች የሚዳኙበት ልዩ ረቂቅ የስነ-ስርዓት ሕግ በጠቅላይ ፍ/ቤት እና በባለድርሻ ተቋማት ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ሕጉ በቅርቡ እንደሚጸድቅ እና ከጸደቀም በኋላ ፍ/ቤቶች በዚሁ ስነ-ስርዓት ሕግ መሰረት እንደሚሰሩ ጠቁመው በሂደት ላይ ያለው የምርጫ ጉዳዮች ስነ-ስርዓት ሕግ እስኪጸድቅ ድረስ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አጭር ቀጠሮ አሰጣጥ ሂደትን በተከተለ መልኩ እና ተገቢ በሆነ ቅልጥፍና እልባት እንዲያገኙ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

 

ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ ሃገራችንን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ለማስጀመር ጠቀሜታ እንዳለው ስለሚገመት ፍ/ቤቶች በብቃት፣ ለሕግ ታማኝነታቸውን እንዲሁም የፍ/ቤቱን ተቋማዊ ገለልተኝነት ለማስመስከር የሚችሉበት እድል እንደሚሆን ያላቸውን ሙሉ እምነት ገልጸዋል፡፡

 

በምርጫ ችሎቶች የመዝገብ አመዳደብን በተመለከተ የምርጫ ጉዳይ መዛግብት መጠን ለየችሎቶቹ እኩል እየተከፈለ የሚመራ መሆኑንም የሰጡት የስራ አቅጣጫ ያመለክታል፡፡

 

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በ2012 በጀት ዓመት መልካም አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዳኞች እና ምድብ ችሎቶች እውቅና ሰጠ፡፡
Next Article የስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት አማካሪ ድርጅት ዕቅድ ዝግጅቱ ያለበትን የስራ ደረጃ ለዐብይ ኮሚቴው ገለጸ
Print
413