በፌደራል ፍርድ ቤቶች የተገልጋዮች የእርካታ ደረጃ በአማካይ 78 በመቶ መሆኑን ጥናት አመለከተ
/ Categories: News

በፌደራል ፍርድ ቤቶች የተገልጋዮች የእርካታ ደረጃ በአማካይ 78 በመቶ መሆኑን ጥናት አመለከተ

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ተገልጋዮች በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያላቸውን የእርካታ ደረጃ ለማወቅ በገለልተኛ ተቋም በተካሔደ የጥናት ግኝት በአማካይ 78 በመቶ የሚሆኑ ተገልጋዮች በአገልግሎት አሰጣጡ እርካታ እንዳላቸው መግለጻቸውን የጥናቱ ውጤት አመለከተ፡፡

ይህም ውጤት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ለተገልጋዮች የእርካታ መመዘኛ ነጥብ ከተቀመጠው 75 በመቶ በላይ የተመዘገበበት በመሆኑ ውጤታማ የሚባል የእርካታ ደረጃ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በሕትመት መልክ የተዘጋጀውን የፌደራል ፍርድ ቤቶች የተገልጋዮች እርካታ ጥናት ሚያዚያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም በተዘጋጀ የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የጥናቱ ውጤት የፍርድ ቤቶች አገልግሎት አድልኦ የማይታይበት፣ በሥነምግባር የሚመራ፣ ግልጽነት ያለው እና ተደራሽ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

ይህም የተረጋገጠው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በተቀመጡ መለኪያዎች የተገልጋዮች እርካታ በአማካይ ከ75 በመቶ በላይ በመሆኑ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በጥናት ውጤቱ የርክክብ ሥነሥርዓት ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር ጥናቱ በገለልተኛ አካል መካሔዱ ከጥናቱ ተአማኒነት ጋር በተያያዘ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን የሚመልስ መሆኑን ገልጸው በጥናቱ ግኝት መሠረት ፍርድ ቤቶች ከውጤታማነት፣ ከቅልጥፍና፣ ከማስረጃ ምዘና፣ ከውሳኔ አሰጣጥ እና ከተያያዥ ጉዳዮች ክፍተት እንዳለባቸው ለተለዩት ክንውኖች ምላሽ ለመስጠት ፍርድ ቤቶች ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ያመላከተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንቶች፣ ም/ፕሬዚደንቶች፣ የችሎት አስተባባሪዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የፍርድ ቤቶቹ ዳኞች እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በዚህ የጥናት ውጤት ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንት እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ ክቡር አቶ ተስፋዬ ንዋይ የጥናቱን ግኝቶች በአምስት ዋና ዋና ምድቦች አቅርበዋል፡፡

እነዚህም በፌደራል ፍርድ ቤቶች ሥነምግባር እና ገለልተኝነት፣ ተደራሽነትና ግልጽነት፣ የአገልግሎት ውጤታማነት፣ ቅልጥፍና እና ተገማችነት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት የፍርድ ቤቶች አፈጻጸም እንዲሁም ባለጉዳዮች ፍርድ ቤት የመጡበትን ጉዳይ የማሳካት ሁኔታን የተመለከቱ ናቸው፡፡

ከእነዚህ የጥናቱ ግኝቶች ውስጥ ሥነ-ምግባር እና ገለልተኝነትን እንዲሁም ተደራሽነትና ግልጽነትን በተመለከተ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተጠቃሚዎች እርካታ ያላቸው ስለመሆኑ ጥናቱ ማሳየቱን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል በአገልግሎት ውጤታማነት፣ ተገማችነት እና ቅልጥፍና ዙሪያ የጥናቱ ግኝት የተጠቃሚዎች እርካታ ከ75 በመቶ በታች መሆኑን ያመላከተ ሲሆን በእነዚህ ዘርፎች ላይ የፍርድ ቤቱ ማሕበረሰብ ትኩረት አድርጎ በመሥራት የተገልጋዮችን ፍላጎት ለማርካት መስራት እንደሚገባ አመላካች ሆኗል፡፡

በክቡር ም/ፕሬዚደንቱ የቀረበውን ማብራሪያ ተከትሎ ከመድረኩ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ሙሉ አቅምን በማውጣት ጥራት ያለው አገልግሎት ማቅረብ፣ ተገማችነት ለማረጋገጥ በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ተመሳሳይ አገልግሎትን ሕግን እና ደንብን ተከትሎ በማቅረብ እንዲሁም ቅልጥፍናን እውን ለማድረግ ያለተደጋጋሚ እና አላስፈላጊ ተለዋጭ ቀጠሮ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ማቅረብ እንደሚገባም በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ፍርድ ቤቱ የዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያከናውነው ሥራ ትውልድን የማነጽ ተግባር እንደሆነ ተጠቆመ
Next Article ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሙስና ተግባራት መከላከያና መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ይፋ አደረገ
Print
36