Tuesday, March 21, 2023 / Categories: News በፌደራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞች ረቂቅ ደንብ ይዘት ላይ ለቋሚ ኮሚቴ አባላት ማብራሪያ ተሰጠ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው የፌደራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞች ረቂቅ ደንብ ይዘት ላይ በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች አማካኝነት ለም/ቤቱ የሕግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ እና ለሰው ሐብት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የስብሰባ አዳራሽ ማብራሪያ ተሰጠ፡፡በረቂቅ ደንቡ ይዘት ላይ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ማብራሪያ የተሰጠው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀደም ሲል ረቂቅ ደንቡን ለዝርዝር ዕይታ ለሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በመራው መሠረት የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ለም/ቤቱ ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ከማቅረባቸው በፊት ረቂቅ ደንቡን በዝርዝር ለማየት በቋሚ ኮሚቴዎቹ በተዘጋጀ የአስረጂ መድረክ (Hearing) ላይ ነው፡፡በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርምርና የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሮን ደጎል 13 ክፍሎች እና 104 አንቀጾች ያለውን ረቂቅ ደንብ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ጠቅለል አድርገው ያቀረቡ ሲሆን የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በበኩላቸው በረቂቅ ደንቡ ድንጋጌዎች ይዘት ላይ ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበው ማብራሪያ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚደንቶች እና ም/ፕሬዚደንቶች እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ቋሚ ኮሚቴዎቹ በተጨማሪም በረቂቅ ደንቡ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግባቸው በሚፈለጉ ነጥቦች ላይ ያሏቸውን ዝርዝር አስተያየቶችና ጥያቄዎች በጽሑፍ በማቅረብ ማሻሻያ በሚያስፈልጋቸው አንቀጾች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ፣ ማስተካከያ እንደማይደረግባቸው በሚታመንባቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ ምክንያቱ ተጠቅሶ በጽሑፍ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴዎቹ በረቂቅ ደንቡ ይዘት ላይ በሚያደርጉት ዕይታ የዳኝነት አካሉን ነጻነት ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ፣ የዳኝነት ሙያ በሌሎች የመንግሥት ተቋማት ከሚሰሩ ሥራዎች አንጻር ሲመዘን የተለየ ባህሪ ያለው መሆኑን እንዲያጤኑ እና የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ተቋማዊ አቅም ከግንዛቤ እንዲያስገቡ አስተያየታቸውን ሰጥተው ረቂቅ ደንቡን ለማሻሻል እንዲረዳ በቋሚ ኮሚቴ አባላቱ የቀረቡ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን በአብዛኛው እንደግብአት የሚወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡የፌደራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞች ረቂቅ ደንብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ተዘጋጅቶ የቀረበው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 39ን መሠረት በማድረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ Previous Article ለፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማነት የዳኞች፣ የአቃቢያነ-ሕግ እና የጠበቆች ሙያዊ ነጻነት ሊረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ Next Article ፍርድ ቤቱ እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ Print 1707