Thursday, November 3, 2022 / Categories: News በፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ እና በሶስት ወር አፈጻጸም ላይ ለቋሚ ኮሚቴ አባላት ማብራሪያ ቀረበ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2015 በጀት ዓመት ዕቅዳቸውን እና የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሶስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም የተመለከተ ማብራሪያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ማብራሪያ አቀረቡ፡፡ ማብራሪያውን ያቀረቡት በቅደም ተከተል የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የፌደራል ሸሪአ ፍርድ ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሲሆኑ ማብራሪያውን ተከትሎ በመድረኩ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ ባለድርሻ አካላት እና ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የፌደራል ፍ/ቤቶች 2015 በጀት ዓመት ዕቅድ የሶስቱም ፍርድ ቤቶች ስትራቴጅክ ስራ አመራር ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን ባሳተፈ ሁኔታ የተዘጋጀና ዕቅዱ በዋነኛነት የፌ/ፍ/ቤቶችን የ2014-18 ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን በ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸም የተገኙ ውጤቶችን በመዘርዘር፣ ያልተከናወኑ ተግባራትን በመለየት፣ ጥንካሬ እና ድክመቶችን በመገምገም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች የተመላከቱበት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል በፍርድ ቤቶች ግልጽ ችሎቶችን ማጠናከር የሕዝብ አመኔታን ከፍ ለማድረግ የሚኖረው የጎላ ሚና የተነሳ ሲሆን በዚህ ዙሪያ በተከናወኑ ተግባራት ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ በፍርድ ቤቶች የተከላካይ ጠበቆች አገልግሎት እየተሻሻለ ስለመምጣቱ የተገለጸ ሲሆን ለዚህ አገልግሎትም በቂ የሰው ኃይል እና በጀት ሊመደብለት እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ የመድረኩ ተሳታፊዎች አንዳንድ ተጠርጣሪዎች ረዥም ጊዜ ታስረው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የሚፈቱበት ሁኔታ ይታያል፣ ተጠርጣሪዎችም በዋስ ተፈትተው በፖሊስ ቁጥጥር የሚቆዩበት ሁኔታ አለ፣ ፖሊስ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ የ14 ቀን ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ የሚጠይቅበት አሠራር እንደችግር አልተጠቀሰም፣ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ ተፈጻሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ምን ያህል ርቀት ይሔዳሉ በሚል ለቀረቡ ጥያቄዎች በፍርድ ቤቶቹ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በሕብረተሰቡ ልዩ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል የሙስና፣ የሰብአዊ መብት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና የሴቶችና የሕጻናት ጉዳዮች በፍርድ ቤቶች በልዩ ትኩረት ሊታዩ እንደሚገባም በቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያ ተሰጥቶበታል፡፡ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደርን የመሳሰሉ አሠራሮች የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ረጅም ጊዜ ይወስዱ የነበሩ ጉዳዮችን የሚያቀላጥፉ አሠራሮች መዘርጋታቸው ውጤት እያመጣ መሆኑ በተሳታፊዎች የተገለጸ ሲሆን በፕላዝማ የሚካሔድ የዳኝነት አገልግሎት አሠራሩን የሚያዘምን ቢሆንም የፕላዝማ አገልግሎት መቆራረጥ እንደተግዳሮት ተነስቶ አማራጭ መፍትሔ እንዲያገኝም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ ከእናቶቻቸው ጋር ወደማረሚያ ቤት የሚላኩ ሕጻናት ለዓመታት በማረሚያ ቤት እንዲያሳልፉ መደረጉ በሥነልቦናቸው ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ ወጣት ጥፋተኞችም በአብዛኛው ጥቃቅን በሚባሉ ወንጀሎች ላይ ተሳታፊ በመሆናቸው በማረሚያ ቤት የሚቆዩ ከሆነም ምቹ ሁኔታ ለፈጠርላቸው እንደሚገባ አስተያየት ቀርቧል፡፡ በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚገኙ የተወሰኑ ዳኞችን ከመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ወደፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ ከፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ደግሞ ወደፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት መድቦ በጊዜያዊነት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉ ስላለው ሕጋዊነት በቀረበ ጥያቄ ላይም ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞች ረቂቅ ደንብ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከአንድ ዓመት በፊት የቀረበ ቢሆንም ባለመጽደቁ ምክንያት የአስተዳደር ሠራተኞች መዋቅር የተጠናቀቀ ቢሆንም ያለዚህ ደንብ ተግባራዊ ማድረግ የማይቻል በመሆኑ ይህ ረቂቅ ደንብ እና የዳኝነት ክፍያ ረቂቅ ደንብ ፀድቀው ሥራ ላይ እንዲውሉ እንዲደረግ በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በኩል ለቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በመድረኩ ላይ በቀረበው የፍርድ ቤቶች የ2015 ዓ.ም ዕቅድ እና የሶስት ወር ሪፖርት ላይ በቋሚ ኮሚቴው የተለያዩ ግብአቶች የተሰጡ ሲሆን ግብአቶችን መሠረት በማድረግ በፍርድ ቤቶች ዕቅድ ላይ ማስተካከያ በማድረግ ለቋሚ ኮሚቴው እንደሚላክ በፍርድ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ግዥን በዕውቀት ሊመሩት ይገባል ተባለ Next Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚደንቶች፣ አመራሮችና ዳኞች ለክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የእንኳን ደስ አለዎት መርሐ-ግብር አካሔዱ Print 2042