በፌደራል ፍ/ቤቶች የአምስት ዓመት ስትራትጅክ ዕቅድ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደ አንድ ግብ የተቀመጠ መሆኑ ተገለጸ
/ Categories: News

በፌደራል ፍ/ቤቶች የአምስት ዓመት ስትራትጅክ ዕቅድ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደ አንድ ግብ የተቀመጠ መሆኑ ተገለጸ

በፌደራል ፍርድ ቤቶች ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው ስትራቴጅክ ዕቅድ ላይ ከተቀመጡ ስድስት ቁልፍ የውጤት መስኮች አንዱ ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት መሆኑንና በዚህ ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደግብ ተይዞ በዚህ ዙሪያ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደት ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ገለጹ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና አስተዳደር ጥናት ኮሌጅ ጋር በመተባበር በሥርዓተ-ጾታና ፍትሕ ተደራሽነት ላይ በተዘጋጁ ሠነዶች ይዘት ላይ ከፍርድ ቤቱ ማሕበረሰብና ከባለድርሻ አካላት ጥሪ የተደረገላቸው 150 ያህል ተሳታፊዎች የተገኙበት አውደ-ጥናት በካፒታል ሆቴል ታሕሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ተካሒዷል፡፡

አውደ-ጥናቱን በንግግር የከፈቱት ክብርት ፕሬዚደንትዋ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ዘርፈ-ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ተቀርጸው ተግባራዊ ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸው በፌደራል ፍርድ ቤቶች ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ እንዲሆን በተዘጋጀው ስትራቴጅክ ዕቅድ ላይ 36 ያህል ፕሮጀክቶች ተቀርፀው በስትራቴጅክ ዕቅዱ ተካትተው ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በአውደ-ጥናቱ ላይ ለባለድርሻ አካላት ውይይት የቀረቡት ሠነዶች በሥርዓተ-ጾታ ኦዲት ሪፖርት፣ በጾታዊ ትንኮሳ መከላከያ እና ቅሬታ አቀራረብ ፖሊሲ፣ በሴት ዳኞች ሜንተሪንግና ኮችንግ ማንዋል እና በጾታዊ ጥቃት ወንጀሎች ክርክር መርሐ-ችሎት መጽሐፍ ላይ ነው፡፡

በእነዚህ ማንዋሎችና መጽሐፍት ላይ የሚሰጡ ግብአቶች ሠነዶችን ለማዳበር እንደሚጠቅሙ የገለጹት ክብርት ፕሬዚደንትዋ፣ ሠነዶቹ ሥራ ላይ ሲውሉ ለሌሎችም መንግሥታዊ ተቋማትም እንደመነሻ (Model) ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የፍርድ ቤቱ ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ባለፉት አራት ዓመታት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ሥርዓተ ጾታን የተመለከቱ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸው ፍርድ ቤቱ ከሥርዓተ ጾታ ጋር በተያያዘ ያሉ አገልግሎቶችን ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ እንዲሆኑ በማስቻል ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠትና በፌደራል ፍርድ ቤቶች ደረጃም ከጾታዊ ትንኮሳ ነጻ የሆነ የፍርድ ቤት ማሕበረሰብ ለመገንባት ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስገንዝበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሥርዓተ-ጾታ ኦዲት እና የጾታዊ ትንኮሳ መከላከያና ቅሬታ አቀራረብ ፖሊሲ ላይ ማብራሪያ ያቀረቡት ወ/ሮ ሳባ ታቢት እና አቶ ዘካሪያስ ፋሲል ሲሆኑ ጾታን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ ወንጀሎች ክርክር መርሐ-ችሎት መጽሐፍን የተመለከተ ገለጻ ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምሕርት ቤት መምሕር እና የሠነዶቹ ዝግጅት አስተባባሪ በሆኑት በዶ/ር ወንድማገኝ ታደሰ ቀርቧል፡፡

በሠነዶቹ ላይ በአዘጋጆቹ የቀረበውን ማብራሪያ ተከትሎ በአውደ-ጥናቱ ተሳታፊዎች ሰፊ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ከቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች መካከል ጠቃሚ የሆኑት ሠነዶቹን ለማዳበር በግብአትነት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ በሰነዶቹ አዘጋጆች ተገልጿል፡፡

በአውደ-ጥናቱ መዝጊያ ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ብርሐነመስቀል ዋጋሪ ባደረጉት ንግግር የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን የዳኝነት አገልግሎት ተፈጻሚና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ መመሪያዎችን ሊያወጣ እንደሚችል በተካተተው ድንጋጌ መሠረት ለውይይት የቀረቡት ሠነዶች ይህን የሕግ ማዕቀፍ መሠረት በማድረግ የተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዛሬው መድረክ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና አስተዳደር ጥናት ኮሌጅ ጋር በመተባበር ለፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች፣ ለሬጅስትራሮች፣ ለአስተዳደር ሠራተኞች እና ከሌሎች የፍትሕ ተቋማት ለተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጾታን መሠረት ባደረጉ የኃይል ጥቃቶች፣ በንቃተ-ሕግና በሴቶች ሰብዓዊ መብቶች፣ ጾታን መሠረት ካደረገ ጉዳት ጋር በተያያዘ በሥነልቦናዊና በማሕበራዊ ድጋፎችና መርሆዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለተከታታይ ሳምንታት ሲሰጡ የቆዩ ሥልጠናዎች እንዲሁም ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ በሥርዓተ-ጾታና ፍትሕ ተደራሽነት ላይ በዝግጅት ሒደት ላይ የነበሩና በአውደ-ጥናቱ ላይ ለውይይት የቀረቡ ሰነዶች ዝግጅት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ፍርድ ቤቱ ከጾታዊ ጥቃት ነጻ የሆነ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ እንዳለዉ ተገለጸ
Next Article በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሕጎችና አዋጆች ሲወጡ ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ
Print
233