በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ትግበራ ማስጀመሪያ ውይይት ተካሄደ
/ Categories: News

በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ትግበራ ማስጀመሪያ ውይይት ተካሄደ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚረዳ የፍትሃ ብሔር ጉዳዩች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ በሚያዚያ ወር 2013 ዓ.ም ማውጣቱን ተከትሎ የመመሪያውን ትግበራ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለማስጀመር የሚያስችል ውይይት ሰኔ 19 ቀን 2013 ተካሄደ፡፡

የፍትሃ ብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር የጉዳዮች መቋጫና እልባት መስጫ ጊዜ መጓተት የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ መቀነስ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት፤       የዳኝነት ነፃነትና ተጠያቂነት ሚዛናዊነት ተጠብቆ ዜጎች ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ ጥራት ያለው የዳኝነት አገልግሎት የማግኘት መብታቸው ተረጋግጦ በዳኝነት ስርዓቱ ላይ ያላቸው አመኔታና እርካታ እያደገ እንዲሄድ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የወጣው የዚህ መመሪያ ተግባራዊ መሆን ጉዳዮች እንደየተናጠል መደባቸውና ባህሪያቸው ተለይተው በተመደበላቸው ጊዜ ገደብ ውስጥ እልባት አግኝተው ባለጉዳዮች በዳኝነት ስርዓቱ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማደረግ፤ እንዲሁም የፍትህ መዘግየትን በማስቀረት በተገቢው ጊዜ ውስጥ ቀልጣፋና ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት የመስጠት ባህል እና አሰራር በመፍጠር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡

የውይይት መድረኩን መልዕክት በማስተላለፍ የከፈቱት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ፉአድ ኪያር በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደርን ለማሻሻል ለረጅም ዓመታት ሲሰራበት የቆየ ቢሆንም ለሶስቱም ፍርድ ቤቶች የሚያገለግል መመሪያ ሳይወጣ መቆየቱን ገልጸው “ዛሬ ትግበራውን ለማስጀመር የምንወያይበት መመሪያ መውጣት የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሆነውን ያልዘገየ ፍትህ ወይም ዳኝነት የማግኘት ጥያቄን ምላሽ የሚሰጥ ነው” ብለዋል፡፡

የመመሪያው ዋና ዓላማ የጉዳዮችን መጓተት ማስቀረት፤ ለሁሉም ጉዳዮች ተገማች ጊዜ ማስቀመጥ፤ ጉዳዮች እንደየመደባቸውና ባህሪያቸው ተመጣጣኝ ትኩረት እንዲያገኙ በማድረግ ዜጎች በዳኝነት ስርዓቱ ላይ ያላቸውን አመኔታ እና እርካታ መጨመር በመሆኑ የፍርድ ቤቱ ዳኞች፤ ረዳት ዳኞች፣ ሬጂስትራሮች እና የስራ ክፍል ኃላፊዎች በመመሪያው አተገባበር ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል ፡፡  

ጠበቆች፤ ተከራካሪ ወገኖች እና ምስክሮች ለመመሪያው መተግበር ያላቸውን ወሳኝ ድርሻ ተረድተው ለዳኝነት ስራ ወጤታማነት የበኩላችውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች፤ ረዳት ዳኞች፤ ሬጂስትራሮች እና የአስተዳደር ክፍል ኃላፊዎች በተሳተፉበት የውይይት መድረክ የመመሪያውን አተገባበር ወጥና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ገለጻ በከቡር አቶ ፉዓድ ኪያር እና በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የልደታ ምድብ ችሎት አስተባባሪ በሆኑት በዳኛ አበበ ሰለሞን ቀርቧል፡፡

የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳር መመሪያ ሰባት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ጠቅላላ ድንጋጌዎች፤ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ዓላማ እና ግብ፤ ስለ ግልጽ ችሎት እና ቀዳሚነት፤ የቀጠሮ ፖሊሲ፤ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር እና የተለያዩ አካላት ተግባርና ኃላፊነት፤ የጉዳዮች እልባት የመስጫ ጊዜ ገደብ፣ ተጠባቂ ግብ እና የጊዜ ገደብ የአፈጻጸም መለኪያዎች፤ እና ልዩ ልዩ ድጋጌዎችን ይዳስሳል፡፡

በውይይቱ ላይ የቀረቡትን ገለጻዎች ተከትሎ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ከቀረቡ አስተያየቶች መካከል የጉዳዮች ፍሰት መመሪያ አተገባበር የአንድ ወቅት ክንውን ብቻ ሆኖ እንዳይቀር በጥንቃቄ ሊከናወን እንደሚገባ ሀሳብ የተሰጠ ሲሆን በተመሳሳይም መመሪያውን ተፈጻሚ ለማድረግ በሚከናወን ጥረት ውስጥ የዳኛና የመዝገብ ቁጥር ያለመመጣጠን፣ የሥራ ግብአቶች ያለመሟላት እና ለመመሪያው አተገባበር አስፈላጊ የሆኑ ምቹ ሁኔታዎች አለመኖር በውጤቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ ከወዲሁ ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም አስተያየት ቀርቧል፡፡

የፍርድ ቤቱ አመራር በበኩሉ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ የፍርድ ቤቱ ወሳኝ የሆነ ሰነድ ነው፡፡ ለአተገባበሩም አመራሩ ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው፤ መመሪያውን ለመተግበር በሚደደረግ እንቅስቃሴ ጉዳዮች እልባት የሚያገኙበትን ጊዜ ለመጠበቅ ሲባል የውሳኔ ጥራት ላይ ችግር እንዳይፈጠር አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በሁሉም የፍትሃ ብሔር ችሎቶች ላይ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያው ተግባራዊ እንደሚሆንና ለዚህም ዳኞች ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ትግበራውን እንዲጀምሩ የፍርድ ቤቱ አመራሮች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ በዚህ ውይይት ላይ ያልተሳተፉ ዳኞችና የአስተዳደር ክፍል ሃፊዎች በቀጣይ ሳምንት የሚወያዩበት መድረክ የሚዘጋጅ መሆኑን ከፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሚካሄድበት ዕለት በከፊል ክፍት ሆነው ይውላሉ፣
Next Article በቅርቡ የፀደቁ የፍርድ ቤቱን አዋጆች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ደንቦችና መመሪያዎች ዝግጅት እየተፋጠነ ነው
Print
2713