በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተቀናጀ የጉዳዮች አስተዳደር መረጃ ስርዓት (ICMIS) እና ኤሌክትሮኒክ-ሰነድ አስተዳደር ስርዓት (e-RMS) ልማትና ትግበራ ጽንሰ-ተልዕኮ (Inception Mission) መርሃ ግብር ተካሄደ
/ Categories: News

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተቀናጀ የጉዳዮች አስተዳደር መረጃ ስርዓት (ICMIS) እና ኤሌክትሮኒክ-ሰነድ አስተዳደር ስርዓት (e-RMS) ልማትና ትግበራ ጽንሰ-ተልዕኮ (Inception Mission) መርሃ ግብር ተካሄደ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን የዳኝነት አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ በራስ-ተግባሪ (Automation) ስርዓት የተደገፈ ለማድረግ የወጠነው ፐሮጀክት በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት- ፍትህ ተግባራት ኢትዮጵያ (USAID- Justice Activities-Ethiopia) ድጋፍ ስርዓቱን ለማልማት በአለም ዓቀፍ ጨረታ ያሸነፈው ሲነርጂ ኢንተርናሽና ሲስተምስ የተባለ ድርጅት ጽንሰ-ተልዕኮ መርሃ ግብር (Inception Mission Schedule ) ከግንቦት 1 -5 ቀን 2014 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዳኝነት አገልግሎቱን በከፍተኛ ደረጃ ራስ-ተግባሪ (Automate) ለማድረግ በተለያዩ ቡድኖች የፍርድ ቤት ጉዳዮች ፍሰት እና ሂደት ጥናት ውጤት ላይ ተመስርቶ የተሰጡ ሁለት ስርዓቶችን አልምቶ የመተግበር ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተቀናጀ የጉዳዮች አስተዳደር መረጃ ስርዓት (Integrated Case Management Information Systems, ICMIS) እና ኤሌክትሮኒክ-ሰነድ አስተዳደር ስርዓት (Electronic-Records Management System, e-RMS) አልምቶ ለትግበራ የሚያዘጋጅ ካምፓኒ ለመቅጠር አለምአቀፍ ግልጽ ጨረታ አውጥቷል፡፡ በሂደቱም ሲነርጂ ኢንተርናሽናል ሲሰተምስ (Synergy International Systems) የተባለ በሁሉም አህጉራት ለሚገኙ ከ80 ሃገራት በላይ ተመሳሳይ ውጤታማ ስራ በመስራት የዳበረ ልምድ ያለው ድርጅት አሸናፊ ሆኖ ተመርጧል፡፡ ይህንን ድርጅት ከሃገራዊ ህግጋትና ከፍርድ ቤቱ ልዩ አገልግሎ አሰጣጥ ባህል ጋር ተያይዞ የሚያማክር ፔራጉዌ (Peragua) የተሰኘ ተጣማሪ ሃገር በቀል ድርጅትም የጨረታው አካል ሆኖ ተቀጥሯል፡፡

በጽንሰ-ተልዕኮ መርሃ ግብሩ በፕሮጀክቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በመሉ ራሳቸውን በጥልቀት የሚያስተዋውቁበት፤ በፕሮጅከቱ ላይ ተመሳሳይ የጋራ አረዳድ እንዲሆራቸው የሚያስችሉ ገለጻዎች፤ በሶስቱም ፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ንድፍ (Business Process Mapping) ግምገማና፣ ቅቡልነት መስጠት፤ በየፍርድ ቤቶቹ ጥቅም ላይ የዋሉ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ቅኝትና ግምገማ ተካሂዷል፤ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የፍርድ ቤቶችን አመራሮች ቁርጠኝነትና መሰረታዊ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችሉ ገለጻዎች ተደርገዋል፤ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ተለይተው ምክክር ተደርገውባቸዋል፡፡

በጽንሰ-ተልዕኮው መርሃ ግብሩ የተሳተፉ አካላት በሙሉ አርብ ግንቦት 5 ቀን 2014 ዓ.ም የማጠቃለያ ውይይት ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንትና ምክትል ፕሬዝደንት ጋር ያደረጉ ሲሆን ሲነርጂ ኢንተርናሽናል ሲሰተምስ (Synergy International Systems) ባለፉት አምስት ቀናት ያደረጓቸው ውይይቶች፣ ቅኝቶች፣ ግምገማዎችና ምልከታዎች ፍሬያማ እንደነበሩ ገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱም የራስ-ተግባሪ (Automation) ስርዓቶችን ለማልማት የሚያስችሉ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በፍርድ ቤት በኩልም የተደረገላቸው ገለጻና ድጋፍ መሰረታዊ መሆኑን ጠቁመው አመራሩ ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ላሳየው ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የራስ-ተግባሪ ስርዓቶች ልማትና ትግበራ ፕሮጀክት (Automation systems development and implementation project) በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት በክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የሚመራ ሲሆን የፍርድ ቤቱ የኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት የማስተባበር ስራውን በተሳካ ሁኔታ እያከናወነ ይገኛል፡፡

በፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል የተባለለት የተቀናጀ የጉዳዮች አስተዳደር መረጃ ስርዓት (Integrated Case Management Information Systems, ICMIS) እና ኤሌክትሮኒክ-መዛግብት አስተዳደር ስርዓት (Electronic-Records Management System, e-RMS) አልምቶ የመተግበር ስራ በነሐሴ /2015 ድረስ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናል ተብሏል፡፡

ለሁለቱ ስርዓቶች መሰረተ ልማት የሆነው የዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ (Wide Area Network, WAN) እና የመረጃ ቋት (Data Center) ግንባታ ስራ ከዚህ ጎን ለጎን እየተሰራ ሲሆን ዕቃ አቅራቢ እና የመዘርጋት አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅትን ለመቅጠር በወጣ ዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ የተሳተፉ ተወዳዳሪዎችን የመለየት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ከኮርት ማናጀር ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሙስና ተግባራት መከላከያና መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ይፋ አደረገ
Next Article ሰበር ሰሚ ችሎቱ ሕጋዊነቱ ባልተረጋገጠ ሁኔታ በእስር ላይ የሚገኙት ኮሎኔል ገሙቹ አያና ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
Print
49