በፌዴራል ፍ/ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት 204 ፋይሎች ታይተው 68 ፋይሎች እልባት ማግኘታቸው ተገለጸ
/ Categories: News

በፌዴራል ፍ/ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት 204 ፋይሎች ታይተው 68 ፋይሎች እልባት ማግኘታቸው ተገለጸ

በፌዴራል ፍ/ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት 204 ፋይሎች ታይተው 68 ፋይሎች እልባት ማግኘታቸው ተገለጸ

በተለያየ የሃራችን ክፍሎች የተፈጠሩ ግጭቶች ጋር በተገናኘ በፌዴራል ፍ/ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት 204 ፋይሎች ታይተው 68 ፋይሎች እልባት አግኝተዋል፡፡

በእያንዳንዱ ፋይል የተከሳሾች ቁጥር በአማካይ ከ 50 – 200 እንደሚድረስ የገለጹት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ ጉዳዩቹ ደግሞ እጅግ ውስብስብ ናቸው ብለዋል፡፡

ክብርት ፕሬዚደንትዋ «ፍርድ ቤቶች እና የሽግግር ፍትሕ፤ ግጭቶች ሲከሰቱ ወይም ከግጭት በኋላ » በሚል ርዕስ በስካይ ላይት ሆቴል ጥር 9 ቀን 2014 ዓ.ም በተዘጋጀ ሲምፖዚየም መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በሀገራችን በተከሰቱ ግጭቶች ሕግንና ሞራልን የጣሱ በርካታ ተግባሮች እንደተከናወኑ ገልጸው በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የተፈጸመው ወንጀል ደግሞ ሊታለፉ ከማይገባቸው ወንጀሎች የሚመደብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ወሲባዊ ጥቃት ወይም የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ዓለም አቀፍ የወንጀል መገለጫዎችን የሚያሟሉ ሆነው ሲገኙ በዓለም አቀፍ ወንጀልነት የሚያስጠይቁ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ሲምፖዚየሙ ከዲያስፖራ ማሕበረሰብ ጋር ውይይት ለማድረግ የተዘጋጀ መድረክ ሲሆን አምስት ፓናሊስቶች በተለያየ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

በአሜሪካን አገር የሕግ ጠበቃና አማካሪ የሆኑት አቶ ደረጀ ደምሴ «ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ግጭቶች ሲከሰቱ ወይም ከግጭት በኋላ ያላቸው ሚና» በሚል ርዕስ ባቀረቡት ማብራሪያ በአሜሪካ በፕሬዚደንት ኒክሰን፣ በፕሬዚደንት ቡሽ እና በፕሬዚደንት ትራምፕ የፕሬዚደንትነት ዘመን ለግጭት መንስዔ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ጉዳዮች ፍ/ቤት በሰጠው ውሳኔ መሠረት ግጭቶቹ ሊመክኑ እንደቻሉ በማስረዳት በአገራችንም የሕዝብ አመኔታ ያተረፉ ፍርድ ቤቶችን መገንባት ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቀረት ስለሚኖረው ፋይዳ አብራርተዋል፡፡

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አብዬ ካሳሁን እና የአፋር ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሙሳ አብድሌ ደግሞ በግጭቱ ምክንያት በየክልሎቻቸው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች በወራሪው ኃይል የደረሰውን ጉዳት በፎቶግራፍ እና በአኃዝ አስደግፈው አቅርበዋል፡፡ በአማራ ክልል በ7 ዞኖች በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ላይ የደረሰውን ውድመት ለመመለስ ከ630 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ በገለጻው የተጠቀሰ ሲሆን በተመሳሳይ በአፋር ክልል ውድመት የደረሰባቸውን ፍርድ ቤቶች መልሶ ለማቋቋም እስከ 300 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ግምት ወጥቶለታል ተብሏል፡፡

የሁለቱ ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶች በግጭቱ ምክንያት የደረሰው ውድመት ዘርፈብዙ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም የዳንነት አገልግሎቱን በዛፍ ጥላ ስርም ቢሆን መስጠት እንጀምራለን ብለዋል፡፡  ፍርድ ቤቶቹን መልሶ ለማቋቋም ግን የሁሉም አካላት ድጋፍ የግድ ነው ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል «የሽግግር ፍትሕ፤ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች» በሚል ርዕስ የሕግ መምሕር የሆኑት ዶክተር ደመላሽ ሽፈራው ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን የሕግ ባለሙያ እና ዕጩ የፒ.ኤች.ዲ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ካሳሁን ይበልጣል ግጭቶች ሲከሰቱ ወይም ከግጭት በኋላ ጾታዊ ጥቃት ያደረሱ ጥፋተኞች ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡

በገለጻቸውም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጀርመን በናዚዎች እንዲሁም በካምቦዲያ እና በሌሎችም አገራት ስለተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች አስካሁን ተጠያቂ የሆነ ሰው ያልነበረ መሆኑን በመጥቀስ አገራችን ለዚህ ጥቃት ትኩረት በመስጠት ወሲባዊ ጥቃት የፈጸሙ ወንጀለኞችን ተጠያቂ ልታደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከመድረክ የቀረበውን ማብረራሪያ ተከትሎ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ነጻና ገለልተኛ ፍ/ቤት፤ ለህግ የበላይነት!

የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ክስ የተቋረጠባቸው ሶስት የክስ መዝገቦች የስነ-ስርዓት ሂደቶች ላይ የተሰጠ የፕሬስ መግለጫ
Next Article ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ
Print
56