በፍርድ ቤቱ ለፍትሃ ብሔር ገዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ አተገባበር ምቹ ሁኔታ ያለ መሆኑ ተገለጸ
/ Categories: News

በፍርድ ቤቱ ለፍትሃ ብሔር ገዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ አተገባበር ምቹ ሁኔታ ያለ መሆኑ ተገለጸ

በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር አስተባባሪ ዳይሬክቶሬት በፍርድ ቤቱ የፍትሃ ብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመተግበር ምቹ አስቻይ ሁኔታ ያለ መሆኑን ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጡን ገለጸ::

አስተባባሪ ዳይሬክቶሬቱ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2013 በጀት ዓመት የፍትሃ ብሔር መዛግብ እልባት ያገኙበትን አግባብ በመመሪያው ከተቀመጠው እልባት የመስጫ ጊዜ ገደብ አንጻር ቅድመ ትግበራ ዳሰሳ ጥናት አካሂዷል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2013 በጀት ዓመት  13,544 የፍትሃ ብሔር ጉዳዮች መዛግብት መከፈታቸውንና 9,983 መዛግብት በበጀት ዓመቱ እልባት/ ውሳኔ ማግኘታቸውን አመላክቷል፡፡  እልባት ካገኙ መዛግብት መካከል  መዛግብት መካከል  8981 መዛግብት በመመሪያው በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ መሰረት እልባት/ ውሳኔ ያገኙ መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡  ይህም በመመሪያው ከተቀመጠው የመዛግብቱ እልባት ማግኛ የጊዜ ገደብ አንጻር አፈጻጸሙን 89.5 በመቶ ያደረሰው ሲሆን የፍርድ ቤቱ አሁናዊ አፈጻጸም ለመመሪያው መተግበር ያለውን መልካም ሁኔታ የዳሰሳ ጥናቱ አሳይቷል፡፡

በፍርድ በቱ የተደራጁት የፍትሃ ብሔር ይግባኝ፤ ሰበር አጣሪና ሰበር ችሎቶች የተናጠል አፈጻጸም ለመዳሰስ በተሰበ መረጃ የሰበር ችሎቱ ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይቷል፡፡ ይህም ወደፊት በተሸሻለው አዋጅ መሰረት ጠበቆች የሚያቀርቧቸው የሰበር አቤቱታዎች የተወሰኑ ከማድረጉ ባሻገር አጣሪ ችሎቱ የማጣራት ስራውን ሲያከናውን ለሰበር ችሎቱ ያስቀርባል የሚባሉት መዛግብት ቁጥር ሊቀንስ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ እየተስተካከለ ሊመጣ እንደሚችል መላምት ተቀምጧል፡፡

በሌላ በኩል የዳሰሳ ጥናቱ በመመሪያው ትግበራ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን ጠቁሟል፡፡  ከስጋቶቹ መካከልም በዳታ ቤዝ የሚገባው መረጃ በመመሪያው ላይ ከተለዩት የጉዳዮች ዓይነት ጋር ያልተጣጣመ መሆኑ፤ የመዛግብት መረጃ በጊዜውና በተሟላ መልኩ በጉዳዮች መከታተያ ዳታ ቤዝ ውስጥ አለመግባቱ፤ የጉዳዮች መከታተያ ዳታ ቤዝ በመመሪያው መሰረት የሚጠየቀውን መረጃ ለይቶ የማይሰጥ መሆኑ የአፈጻጸም ስሌት ስራው በቆጠራ እና በባለሙያዎች ሙሉ የስሌት ስራ ላይ የተመሰረተ መሆኑ፤ የቀጠሮ አሰጣጥ ስርዓት ግልጽና እርግጠኛ አለመሆን ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ የፍትሃ ብሔር ጉዳዮች ዓይነት በመመሪያው መሰረት የሚለይበት ስርዓት መዘርጋት፤ የመዛግብት ወቅታዊ መረጃ በዳታቤዝ የሚገባበትን ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ፤ እና ውዝፍ መዛግብት የሚጣሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ለመመሪያው አተገባበር ውጤታማነት የአመራሩን እና መመሪያውን የሚፈጽሙ ባለሙያዎችን ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ለይቶ አመልክቷል፡፡

በአጠቃላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት የመዝገብ አፈጻጸም አሁን ባለበት ደረጃ እንዲቀጥል ቢደረግ የፍትሃ ብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ አተገባበር ተስፋ ሰጪ ውጤት የሚመዘገብበት እንደሆነ የመመረያውን አተገባበር እንዲከታተልና እንዲያስተባብር የተደራጀው የስራ ክፍል ከዳሰሳ ጥናቱ ውጤት በመነሳት በአጽንኦት ተልጿል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት  

Previous Article በፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ላይ ለዳኝነት ዘርፉ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ
Next Article የ2014 አዲስ ዓመት ጅማሬን አስመልክቶ ከጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ለፌደራል ፍ/ቤቶች ዳኞች የተላለፈ የምስጋና መግለጫ
Print
519