በፍርድ ቤቱ አዲስ ተሿሚ ፕሬዚደንቶች እና በቀድሞ ፕሬዚደንቶች መካከል የሥራ ርክክብ ሥነሥርዓት ተፈጸመ
/ Categories: News

በፍርድ ቤቱ አዲስ ተሿሚ ፕሬዚደንቶች እና በቀድሞ ፕሬዚደንቶች መካከል የሥራ ርክክብ ሥነሥርዓት ተፈጸመ

 

ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት አዲስ በተሾሙ ፕሬዚደንቶች እና በቀድሞ ፕሬዚደንቶች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በተገኙበት በፍርድ ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሔደ ሥነሥርዓት የሥራ ርክክብ ተካሔደ፡፡

ከፍርድ ቤቱ የቀድሞ ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት ከክብርት መአዛ አሸናፊ እና ከክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የሥራ ርክክቡን የፈጸሙት የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 9 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ም/ፕሬዚደንት ሆነው አዲስ የተሾሙት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት እና ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ናቸው።

በሥራ ርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ለእርሳቸውና ለክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ ሀገራቸውን ለማገልገል እንዲችሉ ለሰጡዋቸው አስደናቂ ዕድል ከልብ አመስግነው፣ እርሳቸው ደግሞ የመጀመሪያዋ ሴት የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት የመሆን ዕድል በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በፕሬዚደንትነት ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው አራት ዓመታትም በፍ/ቤቱ ከተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች መካከል ሁለት ዋና ዋና አዋጆችን በማጸደቅ እነዚህን አዋጆች መሠረት ያደረጉ 16 ደንቦችና መመሪያዎች ፀድቀው በሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጉንና በርካታ ረቂቅ መመሪያዎች ተዘጋጅተው ለመጽደቅ በሒደት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

የፍርድ ቤቱ አዲስ ፕሬዚደንት ሆነው የተሾሙት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ኃላፊነት ስለሰጡዋቸው አመስግነው ፍርድ ቤቶች የተጠራቀመና ሲንከባለል የቆየ ችግር የተሸከሙ ተቋማት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በዚያው ልክ የሕብረተሰብ ፍላጎት፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ማሕበራዊ መስተጋብር እየሰፋ ከመሔዱ ጋር ተያይዞ መፍትሔ የሚፈልጉ አለመግባባቶች እንደሚኖሩ አስገንዝበው የማሕበረሰቡን የፍትሕ ፍላጎት ለማርካትና ፍርድ ቤቶች በሕዝብ ዘንድ የሚኖራቸውን አመኔታ ለማሳደግ ተግተው የሚሰሩ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ፍርድ ቤቶች ካለባቸው ችግር አንጻር ደረጃ በደረጃ መፍትሔ ለመስጠት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አዘጋጅተው እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመው በሥራ እንቅስቃሴያቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት አዎንታዊ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article "ፍርድ ቤቱ አገልግሎት ፈላጊዎችን በተሻለ ለማስተናገድ የሚረዱ ስራዎች ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል"-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
Next Article በዳኝነት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከተለመደው አሠራር ወጣ ያሉ አዳዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ
Print
207