Friday, February 24, 2023 / Categories: News በፍርድ ቤቶች መልስ ሰጪን ሳያስቀርቡ ይግባኝን መዝጋት ወይም «አያስቀርብም» በማለት የሚዘጉ መዝገቦችን በተመለከተ የተካሔደ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደረገበት በፍርድ ቤቶች መልስ ሰጪን ሳያስቀርቡ ይግባኝን መዝጋት ወይም «አያስቀርብም» በማለት የሚዘጉ መዝገቦችን በተመለከተ የተካሔደ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደረገበት ********************************************** በመደበኛ ይግባኝ ፍ/ቤቶች እንዲሁም በሰበር ችሎቶች ያለው መልስ ሰጪን ሳያስቀርቡ ይግባኙን መዝጋት ወይም «አያስቀርብም» የሚለው አሠራር በበርካታ የሕግ ባለሙያዎች ቅሬታ የሚቀርብበት አሠራር መሆኑን በመጥቀስ በዘርፉ የተካሔደ አጭር የዳሰሳ ጥናት በፌደራል ጠ/ፍ/ቤት የሕግ ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ አሮን ደጎል ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት እና ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ እንዲሁም ክቡራን የፍ/ቤቱ ዳኞች እና ዋና ሪጅስትራር በተገኙበት የቀረበው የዳሰሳ ጥናት ዓላማ በፌደራል ፍ/ቤቶች በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 337 እና በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ አንቀጽ 28 (1) መሠረት ምክንያቱ ሳይገለጽ ይግባኝን የመዝጋት ወይም «አያስቀርብም» በሚል የሚሰጠው ትዕዛዝ ፍትሐዊነትና ሥነሥርዓታዊነት ላይ ዳሰሳ ማድረግና የተሻለ አሠራር እንዲዘረጋ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ መልስ ሰጪን ሳያስቀርቡ ይግባኝን መዝጋት በሚመለከት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ያለው አሠራር በመደበኛ የይግባኝ ፍ/ቤቶች እና በሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚከናወን የዳሰሳ ጥናቱ ሲቀርብ የተገለጸ ሲሆን በመደበኛ የይግባኝ ፍርድ ቤቶች ያለው አሠራር «አያስቀርብም» ተብሎ መዝገቡ ሲዘጋ የተዘጋበትን ምክንያት ከመግለጽ ጋር በተያያዘ ያለው አሠራር ሁለት መሆኑና አንዱ ምክንያት የማይገለጽበት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ይህም የሚሆነው የዳኞችን ጊዜ ካለው የመዝገብ ክምችት ጋር ለማመጣጠን በማሰብ ሲሆን በሌላ በኩል «አያስቀርብም» የሚባልበትን ምክንያት መጻፍ የስር ፍ/ቤቱን ውሳኔ መድገም ይሆናል በሚል እንደሆነ ጥናት አቅራቢው ገልጸዋል፡፡ በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያለው አሠራር በአዋጁ 28(1) መሰረት አንድ አቤቱታ በሰበር የሚሰማው አስቀድሞ ሶስት የጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኞች ከተመለከቱት በኋላ መሆኑን፣ ችሎቶቹ የ«አያስቀርብም» ትዕዛዝ የሚሰጡት በአንድ ገጽ በተዘጋጀ ቅጽ መሆኑን፣ አጣሪ ችሎቱ «አያስቀርብም» በሚል ምክንያቱን ሳይገልጽ ይግባኙን የሚዘጋው ካለው የሰው ኃይል ዕጥረትና የመዝገብ ክምችት ብዛት አንጻር እንደሆነ በአጣሪ ችሎቱ የሚሠሩ ዳኞች እንደሚያስረዱም አቶ አሮን አስገንዝበዋል፡፡ «አያስቀርብም» ሲባል በምን ምክንያት እንደሆነ አለመገለጹ ከሚያስከተላቸው ችግሮች መካከል ምክንያታዊነትን የማያሟላ እና ለውሳኔ ጥራት ጉድለት ማሳያ መሆኑ፣ የፍርድ ቤት ተአማኒነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ፣ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ መሆኑ አለመታወቁ፣ የፍርድ ምርመራ (Inspection) ሥራን አስቸጋሪ ማድረጉ እንዲሁም ዳተኛ የሆኑ ዳኞች እንዲኖሩ የሚያደርግ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ችግሩን ለማስወገድ የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛ ጊዜ እና በረጅም ጊዜ ሊተገበሩ ይገባል የተባሉ ምክረ-ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ በአጭር ጊዜ እንዲተገበሩ ከቀረቡ ምክረ-ሐሳቦች መካከል የይግባኝ ፍ/ቤት ዳኞች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 337 መሠረት ይግባኙን በሚዘጉበት ጊዜና ሰበር አጣሪ በፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁ. 1234/2013 አንቀጽ 28/1 መሠረት «አያስቀርብም» የሚል ውሳኔ ሲሰጡ በትዕዛዝ መልኩ ሳይሆን ፍርድ በሚጻፍበት መልኩ ሆኖ የሰረዙበትን ምክንያት መጻፍ እንዳለባቸው የሚገልጽ የአሠራር ሰርኩላር መውረድ አንደሚኖርበት በጥናቱ ተመላክቷል፡፡ ምክንያት መጻፍ ከሚያስገኛቸው ፋይዳዎች መካከል ዳኞች ይግባኙን በአግባቡ ስለመመልከታቸው ማረጋገጫ ከመሆኑም በላይ በግዴለሽነት የሚሰጡ ውሳኔዎችን የሚያስቀር መሆኑ፣ በአግባቡ አልታልኝም/ አልተመረመረልኝም የሚል ጥርጣሬን የሚያስወግድ መሆኑ፣ የፍ/ቤት ውሳኔዎችንም ተአማኒ፣ ተገማች እና ምክንያታዊ የሚያደርግ መሆኑ፣ ከአሰራሩ ጋር የተያያዙ የሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን የሚቀንስ መሆኑ፣ በፍ/ቤቶች ያለውን የቁጥጥር እና የተጠያቂነት ሥርዓት የተሻለ የሚያደርግ መሆኑ እንዲሁም ዳተኛ የሆኑ ዳኞችን እንዲቀንሱ የሚያደርግ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ በመካከለኛ ጊዜ እና በረጅም ጊዜ ሊተገበሩ ይገባቸዋል በሚል የተቀመጡ የመፍትሔ ሀሳቦችም በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ Previous Article ለቀድሞዎቹ የፍ/ቤቱ ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት አሸኛኘት ተደረገ Next Article ፍርድ ቤቱ የስድስት ዓይነት መጽሐፍት ድጋፍ ተደረገለት Print 2446