በፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ላይ ለዳኝነት ዘርፉ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ
በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዳኝነት ዘርፉ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላላቸው ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በፍትሐብሔርጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ላይ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ነሐሴ 15 ቀን 2013 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
በሥልጠናው የተሳተፉት ብዛታቸው 65 የሆኑ የፍርድ ቤቱ ረዳት ዳኞች፣ ሴክሬታሪዎች፣ የችሎት ፀሐፊዎች፣ ሬጅስትራሮች እና ዳታ ኢንኮደሮች ናቸው፡፡
ሥልጠናውን የሰጡት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዚደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቦጃ ታደሰ ሲሆኑ ሥልጠናውም በጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ጽንሰ-ሐሳብና መሠረታዊ መርሆዎች ላይ እንዲሁም በቅርቡ በጸደቀው የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 008/2013 ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የሥልጠናው ዓላማ በቅርቡ በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የጸደቀውን ይህን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል ከዳኞች በተጨማሪ ከመዝገብ እንቅስቃሴ ጋር ተያያዥነት ባላቸው የሥራ መደቦች ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች በመመሪያው ላይ በቂ የሆነ መረዳት እንዲኖራቸው በማድረግ ለመመሪያው ተግባራዊነት የሚጠበቅባቸውን የሥራ ድርሻ በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል ነው፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው በፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ዓላማና ግብ፣ በግልጽ ችሎት ዓላማና ግብ፣ በቀጠሮ ፖሊሲ፣ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደርን ተፈጻሚ ለማድረግ የተለያዩ አካላት ተግባር እና ኃላፊነት፣ በጉዳዮች እልባት የመስጫ የጊዜ ገደብ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ሥልጠናውን ተከትሎ ከተሳታፊዎቹ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ በተለይም በፍርድ ቤቱ ከሚገኙ ቢሮዎች አመቺነት፣ ከሥልጠና አስፈላጊነት፣ ባለድርሻ አካላት ከሚኖራቸው አስተዋጽኦ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡
ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ ቦጃ ታደሰ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ክፍተቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ በመጥቀስ ችግሮች እየታዩ አስፈላጊው እርማት እንደሚደረግባቸው ገልጸው የአሠራር ቅልጥፍናን ሊገድቡ በሚችሉ እንቅፋቶች ላይ በሥራ ሒደት በጋራ ማሻሻያና ማስተካከያ እንደሚደረግባቸው አስረድተዋል፡፡
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
316