Friday, January 23, 2026 / Categories: News በ19ኛው የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤቶችና መሰል ተቋማት የሥራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአልጀሪያ አልጀርስ ከተማ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት። የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ በሆኑት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እና በአጣሪ ጉባዔ ጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር በአቶ ደሳለኝ ወዬሳ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ማክሰኞ ጥር 12 ቀን 2018 ዓ.ም አልጀርስ ሲደርስ በአልጀሪያ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤት ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። በ19ኛው የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤቶችና መሰል ተቋማት የሥራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ አልጀሪያ ያቀናው የኢትዮጵያ ልዑክም ትናንት ረቡዕ ጥር 13 ቀን 2018 ዓ.ም የአልጀሪያን ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤት፣ የአልጀሪያን ጠቅላይ ፍ/ቤት እና የአልጀሪያ ዳኞች ማሰልጠኛ አካዳሚን እንዲጎበኝ በተያዘው መርሃ ግብር መሰረት፤ የአልጀሪያ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት ፍ/ቤት በመገኘት ስለ አሠራሩ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ከኢትዮጵያ አቻ ተቋማት ጋርም የልምድ ልውውጥም ተደርጓል። በተጨማሪም ልዑካን ቡድኑ የአልጀሪያ ጠቅላይ ፍ/ቤትን የጎበኘ ሲሆን ከአልጀሪያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት ጋር ውይይት ተደርጓል። በዚህም በዲጂታል ኮርት ሲስተም ላይ በየችሎቱ በመገኘት የልምድ ልውውጡን ያደረገው የኢትዮጵያ ልዑክ የኢትዮጵያን ተሞክሮም ለአልጀሪያ አቻ ተቋማት አጋርቷል። በክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ጉብኝቱን በመቀጠል በአልጀሪያ የዳኞች ማሰልጠኛ አካዳሚ በመገኘት የአካዳሚው የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ስል ስልጠና ክፍሎቹ እና ስለ ጠቅላላ አሠራሩ ገለፃ እና ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል። የልዑካን ቡድኑ ዛሬ ጥር 14 ቀን 2018 ዓ.ም ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፈው ህዳር ወር በስኬት ያስተናገደችውን 4ኛውን የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤቶች እና መሰል ተቋማትን ሲምፖዝየም ፕሮሲዲንግ ሪፖርት ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እንደሚቀርብ የደረሰን መረጃ ያመላክታል። ሀገራችን ኢትዮጽያ የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤቶችና መሰል ተቋማት አባል ከመሆኗ ባሻገር በሀገራችን ኢትዮጵያ በፍትሕ ሥርዓቱ ዙሪያ የመጀመሪያ የሆነውን አህጉር አቀፍ መድረክ በስኬት ማስተናገዷ ይታወሳል። Previous Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢኮርት ትግበራ ላይ ለፍትህ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ገለጻ ተደረገ Next Article የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማህበር አመራሮች በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውይይት እና ጉብኝት አደረጉ Print 454