ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱ ተገለጸ
/ Categories: News

ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱ ተገለጸ

 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች እየተከናወኑ ባሉ የማሻሻያ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መገኘታቸውን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞችና የአስተዳደር ዘርፍ ሃላፊዎች እንዲሁም የስር ፍርድ ቤቶች ፕዝደንቶችና ም/ፕሬዝደንቶች በተገኙበት በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ገለጹ፡፡

የውይይት መድረኩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል- ፐሪዝን ፌሎው ሺፕ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሂደት የፍርድ ቤቶች ሚናን አስመልክቶ ዳኞች በሙያቸው ያገኙትን ዕውቀትና እና አመለካከት እርስ በእርስ እንዲለዋወጡ ማስቻል እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የማሻሻያ ስራዎች ያስገኙትን ውጤት መገምገም ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

ክብርት ፕዝደንቷ ባለፉት ሶሰት ዓመታት ተግባራዊ በተደረጉት የፍርድ ቤቶች የማሻሻያ ስራዎች የፌዴራል ፍርድ ቤቶች እና የዳኝነት አስተዳደር አዋጆች መሻሻላቸውን እንዲሁም የፍርድ ቤቶቹን ተቋማዊና የዳኞችን ግለሰባዊ ነጻነት ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች የዳኝነት ነጻነት አንጻራዊ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተልዕኮ እና ተፈጥሯዊ ባህሪ የሚገልጽ ዓርማ ተቀርጾ ጥቅም ላይ መዋሉ፤ እና ውጤት አምጪ የአሰራር ስርዓትና አደረጃጀት ለመዘርጋት የሚያስችሉ የዳኞች ስነምግባርና ዲሲፕሊን ክስ አቀራረብ ደንብ እና የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያዎች ጸድቀው መተግበር መጀመራቸው ተጠያቂነት ስርዓት ጠበቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር ቀልጣፋ ዳኝነት እንዲሰጥ አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከብርት ወ/ሮ መዓዛ በንግግራቸው በኮሚዪኒኬሽን ዘርፍ ወደ ህዝቡ ለድረስ በመደበኛና ማህበራዊ ሚዲያ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም ፍርድ ቤቶች የሚሰሯቸውን ስራዎች በማስተዋወቅና የህዝቡን ሚዛን ያልጠበቀ አመለካከት ከማስተካከል አንጻር ውስንነት ያለ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ስራዎችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ ከለጋሽና አጋር አካላት ጋር አጋርነት በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ውጤት ያስገኙ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው የአገልግሎት፣ የሙያ እና የክህሎት ማዳበሪያ ድጋፎች መገኘታቸውን አብራርተዋል፡፡

ፍርድ ቤቶችን በቡድን መምራትና ኃላፊነትን መወጣት አዲስ የተገነባና የማሻሻያው ውጤታማነት አንዱ ማሳያ መሆኑን ያመለከቱት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ በሶስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተናበበ እና የጋራ ግብን ማሳካት የሚያስችል አመራር በመስጠት፣ አፈጻጸሙን በመከታተልና በመደገፍ ትልቁን ሚና የተጫወቱ የለውጥ አመራሮችን አመስግነዋል፡፡

በዚሁ መድረክ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የህግ የበላይት እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የወደፊት ትኩረት በሚል ርዕስ ገለጻ አቅርበዋል፡፡ ክቡር አቶ ሰለሞን በገለጻቸው መጀመሪያ ምዕራፍ በፍርድ ቤቱ ተጠንተው ለትግበራ የተዘጋጁ ፐሮጀክቶችን ያነሱ ሲሆን በዋናነት የፍርድ ቤቱን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ (Automate) ለማድረግ በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት-ፍትህ ፕጀክት- ኢትዮጵያ ድጋፍ የእየተሰራ ያውን ስራ ያለበትን ደረጃ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቶችንም በዋይድ ኤሪያ ኔት ዎርከ ለማስተሳሰርም በተያዘው ፕሮጀክት የዳታ ሴንተር ግንባታ እና ተያያዥ ስራዎች በአማካሪ ድርጅት እየተተገበሩ መሆኑን አሳይተዋል፡፡ ከብራንዲንግ ስራ ጋር ተያይዞ የዳኞች ጋወን እና የችሎት አደረጃጀት ስታንደርድ እንዲሁም ከፕሮቶኮል ጋር በተያያዘ ጠናቱ ተጠናቆ ለትግበራ መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል፡፡

ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በገለጻቸው ሁለተኛ ክፍል የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የፍርድ ቤቶችን ሚና አብራርተዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች ህግን መሰረት ያደረገ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ግልፅ፣ ጥራት ያለው እና ተገማች ዳኝነት በመስጠት የህግ የበላይነትን ያረጋግጣሉ ያሉት ክቡር አቶ ሰለሞን፤ የዳበረ የዳኝነት ስርዓት የገነቡ ሃገራትን በተለይም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን ልምድ በመጥቀስ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በሃራችን የፍትህና የዳኝነት ስርዓት በምን ደረጃ ላይ ነን ብላችሁ ራሳችሁን ትገመግማላችሁ የሚል ጥያቄ በማንሳት እና ዳኞች በእያንዳንዱ ውሳኔያቸው ለፍትህ ስርዓቱ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለራሳቸው እንዲመለከቱ ሃሳብ በማቅረብ ገለጻቸውን አጠናቀዋል፡፡

በውይይት መድረኩ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሬጂስትራር ስራዎች ማሻሻያ እና በአስተዳደር ዘርፍ ማሻሻያ ስራዎች የተከናወኑ ተግባራትን እና የተገኙ ውጤቶች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቦጃ ታደሰ እና በኮርት ማናጀር አቶ ነሞ አዱኛ ቀርቧል፡፡

የጀስቲስ ፎር ኦል ፐሪዝን ፌሎው ሺፕ ፕሬዝደንት ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ ድርጅታቸው በዳኝነት ዘርፉ ላለፉት 20 ዓመታት ድጋፎችን ሲያድርግ የቆየ መሆኑን ተናግረው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ /ፍርድ ቤት መር አስማሚነት/ የዳኞች ስነምግባር ደንብ እና የዳኞች የስራ አፈጻጸም ምዘና መመሪያ እና በመሳመሰሉት ቀደም ሲል በጀስቲስ ፎር ኦል ተጀምረው በአዲሱ አመራር ደግሞ እየተጠናቀቁ ወደ ትግበራ ምዕራፍ በመግባታቸው ያላቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሚያከናውናቸው የማሻሻያ ስራዎችም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያድርግ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ክብርት ወ/ሮ መዓዛ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችና የአስተዳደር ሰራተኞች ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ሃገራችን በገጠማት ወቅታዊ ችግር ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው ለተፈናቀሉና በችግር ላይ ላሉ ወገኖች ድጋፍ በማድረጋቸው አመስግነዋል፡፡

ነጻና ገለልተኛ ፍ/ቤት ለህግ የበላይነት!

ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

ታህሳስ 9 ቀን 2014 ዓ.ም

Previous Article ፍርድ ቤቱ በስትራቴጂያዊ እና ዓመታዊ ዕቅዱ ላይ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ማብራሪያ ሰጠ
Next Article ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፌዴራል ፍርድ ቤት መር አስማሚነት መመሪያ አወጣ
Print
160