ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ግዥን በዕውቀት ሊመሩት ይገባል ተባለ
/ Categories: News

ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ግዥን በዕውቀት ሊመሩት ይገባል ተባለ

የግዥን ጉዳይ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በዕውቀት ሊመሩት ይገባል ሲሉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ ገለፁ፡፡

በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አዘጋጅነት ለዳኝነት አካላት በአርባ ምንጭ ከተማ ሲሰጥ በነበረው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ የተገኙት ምክትል ፕሬዝዳንቱ በአብዛኛው በከፍተኛ አመራሮች ላይ የሚቀርቡ የሙስና ወንጀል ክሶች ከግዥ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ከፍተኛ አመራሮች ግዥን በዕውቀት ሊመሩት ይገባል ብለዋል፡፡

ግዥ ከዕለት ዕለት ስራዎቻችን ጋር የሚገናኝ ነው ያሉት ም/ፕሬዝዳንቱ፣ በተለይ ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው የግዥ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡ ክሶችን ሀገራዊ ፋይዳቸውን በመረዳት በሚገባና ወቅቱን በጠበቀ መልኩ የተፋጠነ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በመከተል የሀገርን ኢኮኖሚ መታደግ እንደሚገባም አስምረውበታል፡፡

ክቡር ም/ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት ሀገራችን ካላት ውስን ሀብት 60 በመቶ የሚሆነው ለግዥ የሚውል መሆኑን መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ገልጠዉ ዘርፉ ከፍተኛ ሀብት የሚያስተናግድ እንደመሆኑ መጠንና ለሙስና ተጋላጭ በመሆኑ በልዩ ትኩረት መታየት ይገባዋል ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቶች ከመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አኳያ ድርብ ኃላፊነቶች ያሉባቸዉ እንደመሆኑ መጠን ከግዥ አኳያ ወደ ተቋሞቻችን የሚመጡ ጉዳዮችን የጉዳዮቹን ክብደት፣ ውስብስብነት፣ አስቸኳይነትና ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ ማስተላለፍ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤት በሕገ መንግስቱ መሰረት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ እንደመሆኑ መጠን ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ጥራት ያለው የዳኝነት አገልግሎት መስጠትና በግዥ ዙሪያ ያሉ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እንዲሁም የአሰራር ስርዓቶች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በሚገባ በመመርመርና አሰራሮችን በማወቅ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መስጠት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም መፍጠር እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

ምንጭ፡- የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

Previous Article የሌሎችን  የሥነምግባር ችግር ከሚዳኘው የዳኝነት ተቋም የላቀ የሥነምግባር ደረጃ እንደሚጠበቅ ተጠቆመ
Next Article በፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ እና በሶስት ወር አፈጻጸም ላይ ለቋሚ ኮሚቴ አባላት ማብራሪያ ቀረበ
Print
2093