ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ
/ Categories: News

ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ

ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ (የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንት) ጥር 9 ቀን 2014 ዓ.ም «ፍርድ ቤቶች እና የሽግግር ፍትሕ፤ ግጭቶች ሲከሰቱ ወይም ከግት በኋላ» በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ ከተሳታፊዎች የቀረቡ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን መሠረት በማድረግ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ፡-

• ሲምፖዚየሙን ማዘጋጀት ያስፈለገው አሁን አገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ የዳኝነት ተቋሙ ሊኖረው ከሚችለው የዳኝነት ሚና ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

• በአገራችን ለውጥ ከተጀመረበት ከባለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ፍርድ ቤቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሥራዎቻቸውን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ለዚሀም በቅርቡ በአማራ እና በአፋር ክልል ፍርድ ቤቶች የደረሰባቸው ውድመት እና የክልሎቹ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንቶች የተገለጿቸው ማሳያዎች ናቸው፡፡

• በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ የክልልም ሆኑ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ነጻነትን ከማረጋገጥ አንጻር፣ በውስብስብና በግለሰብ መብቶች ላይ ከመንግስት አቋም የተለየ የሆኑና አስተማሪ ውሳኔዎች መወሰን መጀመራቸው የፍርድ ቤቶች መሻሻልን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡

• የግለሰብ መብቶችን የጣሱ የመንግሥት አካላትን በመክሰስ እነዚያ መብቶች እንዲረጋገጡ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ (Legal Framework) መዘጋጀቱን፣ የአስተዳደር አካላት ውሳኔዎች በፍ/ቤት እንዲከለሱ ለማድረግ የተሰራው ሥራ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወነ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

• የህዝብ አመለካከትን በተመለከተም በዩ.ኤስ.ኤይድ (USAID) በኩል አጥኝ ድርጅት ተቀጥሮ በጥናቱ ውጤትም ትልቅ መሻሻል መኖሩን የሚያሳይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

• ሀገራችን ከግጭት ዑደት ለመውጣት ጠንካራ ፍ/ቤቶች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ጠንካራ ፍርድ ቤት ለመሆን ደግሞ የፍ/ቤቱን አቅም መገንባት (Empower)፣ ተፈጥሮአዊ የሆነውን የፍ/ቤት ሥራ እንዲሰራ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ይህ ከተደረገ ደግሞ ሰዎች በፍ/ቤት ይጠቀማሉ፤ ፍርድ ቤት በሚወስናቸው ውሳኔዎች ላይ አመኔታ (trust) ይኖረዋል፡፡ እነዚህን እና መሰል ጉዳዮችን መመዘን እንደሚገባ አንስተዋል፤

• በመንግሥት አካላት ማለትም በሕግ አውጭው፣ በሕግ ተርጓሚው እና በዳኝነት ዘርፉ መካከል ክርክር ቢፈጠር ጉዳዩ በፍ/ቤት መታየት አለበት፡፡ በሀገራችን የግጭት ዑደት እንዲኖር የሚያደርገው የሥልጣን ፍጭት ነው፡፡ የስልጣን ፍጭት በመንግሥት አካላት መካከል፣ በክልልና በፌደራል መንግሥት ባሉ አካላት መካከል ሲፈጠር መፍትሔው ወደ ፍርድ ቤት መምጣት ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ ፍርድ ቤቶች የዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ሚና አላቸው ወይስ ፍ/ቤቶች ሚና ስለሌላቸው ሰዎች ችግሩን ለመፍታት ወደሌላ አማራጭ ይሄዳሉ? በሌሎች አገራት ጦር ሊያማዝዙ የሚችሉ ችግሮች ወደፍርድ ቤት ቤት እየመጡ የሚስተናገዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

• ፍ/ቤቶች የዛሬውን ግጭት ለመፍታት ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ ተመሳሳይ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግ ምን ዓይነት ሚና ሊኖራቸው ይገባል? በምን ዓይነት መልኩ መደራጀት አለባቸው? በሚለው ነጥብ ላይ ከዚህ በኋላ በሚካሄዱ መድረኮች ላይ ሀሳቦች እንዲነሱ የማድረግ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

• ወደፊት አገራችን በዚህ ሁኔታ አንዱ በጉልበት «መብቴን አስከብራለሁ» የሚልባትና ሌላው ደግሞ ይህን ለማስቆም ወደሌላ ግጭት እና ውድመት የሚገባበት ሁኔታ ሊቆምና በዚህ ላይ የፍ/ቤቶች ሚና ወሳኝ ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

• ፍርድ ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው በአማራ፣ በአፋር እና በትግራይ ክልሎች ብቻ ሳይሆን በደቡብ እና በሌሎችም ክልሎች በሕዝባዊ አመጽ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የዚህም ሰለባ መሆናቸውን፣ በጉዳቱም የፍ/ቤቶች የማስቻያ ቦታዎች እና ሌሎች ግብአቶች የወደሙ በመሆኑ ሥራ ለማስቀጠል በማይቻልበት ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው፡፡ በዳኞች ሕይወት እንዲሁም በሠራተኞች ላይ አካላዊና የስነልቦና ጉዳትም ደርሷል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ወጥተን እንዴት ሥራ ልንጀምር እንችላለን? የሚለው ጉዳይ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ፍርድ ቤቶች እንደገና ተቋቁመው ሥራ ሊጀምሩ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ፍርድ ቤቶች እና መንግሥት ሊወስዱት የሚገባ ድርሻ ያለ ከመሆኑም በላይ በአገራቸው ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ከአገር ውስጥና ከውጭ የመጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

• በግጭት ወቅት የተፈጸመውን ጾታዊ ጥቃት በተመለከተ በቅድሚያ ከዳኝነቱ አካል ውጭ ያሉ ሉሎች አካላት በስፋት ሊሰሩበት ይገባል፡፡ ይህን ጉዳይ መፍትሔ ካልተሰጠውና በአጥፊዎች ላይ እርምጃ ካልተወሰደና ውሳኔ ካልተሰጠው እንደሀገር የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት አልተወጣችሁም የሚል ዓለም አቀፍ ተጠያቂነት ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

ነጻና ገለልጸኛ ፍ/ቤት፤ ለሕግ የበላይነት!

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article በፌዴራል ፍ/ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት 204 ፋይሎች ታይተው 68 ፋይሎች እልባት ማግኘታቸው ተገለጸ
Next Article የዳኝነት ስርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ፍርድ ቤቱ ከማህበሩ ጋር አብሮ እንደሚሰራ ተገለጸ
Print
48