ወጥነትና ተገማችነት በሌላቸው የሰበር ውሳኔዎች እና የወደፊት አቅጣጫ ላይ የውይይት መድረክ ተካሄደ
/ Categories: News

ወጥነትና ተገማችነት በሌላቸው የሰበር ውሳኔዎች እና የወደፊት አቅጣጫ ላይ የውይይት መድረክ ተካሄደ

ወጥነትና ተገማችነት በሌላቸው የሰበር ውሳኔዎች እና የወደፊት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በቀን 01/13/2017 ዓ.ም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮችና ዳኞች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

መርሃግብሩን በንግግር የከፈቱት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ለማህበራዊ ሥርዓት መሠረት ተደርጎ የሚወሰድ እና በሕዝብ የታመነ ፍርድ ቤት ሊያሳካ ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ ተገማች ውሳኔ መስጠት መሆኑን ጠቁመው የተገማችነት ጉዳይ የሕግ ትክክለኝነት መታወቅ እና ምክንያታዊ ውሳኔ መኖርን እንደ ግብ በመያዝ ዜጎች ዛሬ የሚያደርጉት ድርጊት ነገ የሚኖረውን ውጤት መተንበይ እንዲችሉ እንዲሁም በፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ውሳኔዎች ነገ የሚያስከትሉትን ውጤት ለማወቅ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቶች ተገማች ውሳኔ ካልሰጡ በእኩልነት የመዳኘት መብትን የሚጋፋና የግልፅነት መርህን የሚፃረር ከመሆኑም በላይ የፍርድ ቤቶችን ተአማኒነት የሚሸረሽር በመሆኑ በጥናት በተለዩት ችግሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመወያየት የፍርድ ቤቱን ራዕይ ለማሳካት የሚያስችል አሠራር በመዘርጋት የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ለውይይቱ መነሻ እንዲሆን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክቡር ዳኛ ተሾመ ሽፈራው ወጥነትና ተገማችነትን በማረጋገጥ ረገድ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ውሳኔዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚዳስስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች በሁሉም ፍርድ ቤቶች አስገዳጅነት ያላቸው በመሆን በአገሪቱ ወጥ እና ተገማች የሕግ አተገባበር እንዲኖር በማድረግ በሀገሪቱ ሥነ ህግ እድገት ላይ ያሳረፈው አሻራ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ቢሆንም በተለያየ መልኩ ከተገልጋዮችና የህግ ባለሙያዎች ከሚነሱ ችግሮች አንዱ ወጥነት የሌላቸው የህግ ትርጉም የያዙ ውሳኔዎች ይሰጣሉ የሚል መሆኑ እና ይህም ችሎቱ የተቋቋመበትን ወጥ እና ተገማች የሆነ ውሳኔ የመስጠት አላማን የሚያፋልስ ከመሆኑም በላይ ማህበረሰቡ በፍርድ ቤቱ እምነት እንዲያጣና ዳኞች ላይም ብዥታን የሚፈጥር በመሆኑ ችግሩን በግዜ ለመቅረፍ እንዲያስችል የዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ የመነሻ ጽሁፍ ሊቀርብ እንደቻለ በጥናቱ ላይ ተመላክቷል፡፡

ክቡር ዳኛ ተሾመ ሽፈራው ባቀረቡት ገለጻና ማብራሪያ ላይ ከቀረቡና ዳሰሳ ከተደረገባቸው በርካታ የሰበር ውሳኔዎች መካከል የወንጀል ጉዳዮች፣ የስራ ክርክር፣ የውርስ ጉዳዮች፣የባልና ሚስት ንብረት ክርክር፣ ፍቺ፣ ዳግም ዳኝነት ፣ ሌሎች የፍትሐብሄር ሥነ ስርዓት ህግን የተመለከቱ ጉዳዮች እንዲሁም የፍርድ ቤቶች ስልጣንን በተመለከተ የተወሰኑ ወጥነት የሌላቸው የሰበር ውሳኔዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡በውይይቱም በርካታ ሃሳቦች ተነስተው የመፍትሄ ሃሳቦችና የወደፊት አቅጣጫዎች ማስቀመጥ ተችሏል፡፡

መድረኩ የተዘጋጀው በUNDP የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡

Previous Article የቪድዮ ኮንፍረንስ፣ ኢ- ፋይሊንግ እና ዳታቤዝ አገልግሎት በደቡብ ምዕራብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ቦንጋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይፋ ተጀመረ
Next Article በኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቆይታ ያደረጉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ልምዳቸውን አካፈሉ
Print
356