Monday, December 30, 2024 / Categories: News ዓለም አቀፍ የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከበረ ዓለም አቀፍ የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ‹‹የሴቷ ጥቃት የኔም ነዉ፣ ዝም አልልም›› በሚል መሪ ቃል የፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች፣ ከፍትህ ተቋማት የተገኙ ሃላፊዎች፣ የመንግስት ሆስፒታሎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ታህሳስ 18 ቀን 2017 ዓ/ም ተከብሯል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ፣ በሃገራችን ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ እየተከበረ በሚገኘው የጸረ ጾታዊ ጥቃት ቀን ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር ወ/ሮ ዙፋን ወ/ገብርዔል ጾታዊ ጥቃት ከፍተኛ የሆነ የአካል፣ የአእምሮ፣ የስነ-ልቦናና የማህበራዊ ቀዉሶችን በተጎጂዎች/ተጠቂዎች ላይ በማድረስ በነጻነት እንዳይኖሩ፣ ማንነታቸዉ እንዲዋረድ፣ ደህንነታቸዉ በስጋት ላይ እንዲወድቅ በማድረግ ከፍተኛ የህይወት ዘመን ቀዉስ/ጉዳት እንደሚያደርስ ገልጸዉ እነዚህና ሌሎች ለህብረተሰብ መብት ጥሰት ምክኒያት የሆኑትን ያልተገቡ ድርጊቶች ለመከላከልና ተፈጽሞም ሲገኙ ምላሽ ለመስጠት ያስችል ዘንድ የተለያዩ ህጎችንና ፖሊሲዎችን በማዉጣት ለተግባራዊነታቸዉም መረጋገጥ አደረጃጀቶችንም ሆነ ሌሎች ስልቶችን በመንደፍ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶችም የዚሁ አደረጃጀት አንዱ አካል በመሆናቸዉ ከተሰጣቸዉ ስልጣንና ተግባር አንጻር ጾታን መሰረት በማድረግ የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ለሚቀርቡ ክሶች ፍትሃዊ የሆነ ዳኝነት ለመስጠት እንዲቻል የተለያዩ ፕሮግራሞችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ፣ አዳዲስ የአሰራር ስርዓቶችን በማዉጣት የተሻለ አሰራር በመዘርጋት የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡ የህዝብ አመኔታ ያለዉ እንዲሆን ትልቅ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው በተለይም በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መነሻነት ወደ ፍርድ ቤቱ የሚቀርቡ ጉዳዮች ተገቢ ዉሳኔ ለመስጠት የሚያስችሉ የሴቶችና ህጻናት ችሎት በማደራጀትና መሰል በርካታ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ወርቅነሽ በቀለ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያየ መልኩ በሴቶች ላይ የሚፈጸመዉ አስከፊና የሃይል ጥቃት እንዲቆም ለማድረግ የተለያዩ ንቅናቄዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸው ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት የሰብዓዊ መብት ጥያቄ መሆኑን ግንዛቤ ለመፍጠር፣ መንግስታት የሃይል ጥቃትን ለማስወገድ የገቡትን ቃል እንዲጠብቁ ጫና ለመፍጠር፣ በየአከባቢዉ የሚደረጉ የጸረ ጾታ ጥቃት ትግሎችን ለማጠናከር፣ የጾታ ጥቃትን ለማስወገድ የሚንቀሳቀሱ ኣካላትን ህብረት ለማጎልበትና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለማስወገድ ቀኑ ተከብሮ ይውላል ብለዋል፡፡ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች በስፋት እንደሚፈጸምና የዚህ ድርጊት ዋነኛ ተጎጂዎች ሴቶችና ህጻናት እንደሆኑ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ገልጸው በፍትህ አሰጣጥ ሂደት ዙሪያ ያሉ መልካም ተግባራትን ለማጠናከርና ክፍተቶችን በመሙላት በቀጣይ የተሻለ ዉጤት ማምጣት ለማስቻል እንዲህ አይነት መድረኮች ጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሴቶችና ህጻናት ወንጀል ችሎት ዳኛ የሆኑት ክብርት ዳኛ ምህረት መላኩ የፍርድ ሂደት ሁኔታ፣ተግዳሮትና መልካም ተሞክሮን አስመልክቶ ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን በአዲስ አበባ ፖሊስ የሴቶችና ህጻናት ላይ ሚፈጸሙ ወንጀሎች ምርመራና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አለማየሁ ንጋቱ የጾታዊ ትቃት የፍትህ ሂደት በአዲስ አበባ ፖሊስ በርካታ ተሞከሮዎች ላይ ገለጻ አቅርበዉ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ Previous Article ሀገር አቀፍ የህግ ተርጓሚዎች መድረክ ተካሂዷል Next Article በኢፋይሊንግ፣ ኢሊቲጌሽን እና ኤሌክትሮኒክ ሪከርድ አመራር አፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ ላይ የውይይት መድረክ ተካሄደ Print 1165