Monday, December 16, 2024 / Categories: News ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከበረ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ፣ በአገራችን ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ "ወጣቶችን ያማከለ የፀረ-ሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል" በሚል መሪ ቃል በመከበር ላይ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን ታህሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ ቤቱ ዳኞችና የአስተዳደር ሠራተኞች በተገኙበት ተከብሯል፡፡ ቀኑን አስመልክቶ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ድሪባ ፈዬራ በየዓመቱ አገራት በሙስና የሚገኙበትን ደረጃ የሚያወጣው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እ.ኤ.አ በ2023 ባወጣው ደረጃ ከ180 አገራት ኢትዮጵያ 98ኛ መሆኗን ጠቅሰው ይህም ሙስናን በመዋጋት ረገድ እንደሀገር ብዙ የሚጠበቅብን መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ በፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከሙስና ጋር በተያያዘ ከሕብረተሰቡ የሚሰነዘረውን ወቀሳ ለማስቀረት ሰፊ ትግል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንና ሙስናንን በአመት አንድ ጊዜ በሚካሔድ እንቅስቃሴ ማሻሻል እንደማይቻልና ይልቁንም በየቤቱ ልጆች ሙስናን እንዲጠየፉ ከማስተማር ጀምሮ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ ላይ በትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ለተሳታፊዎች በዲሲፒሊን ምንነት፣ በወሳኝ አስተሳሰብ (Critical Thinking)፣ በዕውቀት፣ ችሎታ እና አመለካከት (Knowledge, Skill and Attitude) ጽንሰ-ሐሳብ፣ እንዲሁም በፍትሕ ዘርፍ አገር በቀል ዕውቀት ስለሚጫወተው ሚና፣ የግል ሥነምግባር እና ሙያዊ ሥነምግባር ምንነትና እነዚህን ማሻሻል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ፣ በአመራር ጽንሰ-ሐሳብ (Leadership) ላይ ያተኮረ ሰፊ ማብራሪያ የመድረኩን ታዳሚዎች ባሳተፈ ሁኔታ አቅርበዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ዘርፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ነሞ አዱኛ በመድረኩ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት መልካም ሥነምግባር የነገውን ትውልድ ስብዕና የሚገነባ መሆኑን ጠቅሰው ይህን ለማረጋገጥ ሁሉም ድርሻውን በመወጣት መልካም ሥነምግባርን ለቀጣዩ ትውልድ በተግባር ማሳየትና ምሳሌ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ክቡር ዳኛ ቀንዓ ቂጣታ በበኩላቸው የሙስና ድርጊት በአንድ አገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ውጤት በመግለጽ በተለይ በፍርድ ቤቶች የሚታይ የሙስና ድርጊት ዳኝነት የሚሰጠው ሕግና ሕግን ብቻ መሰረት አድርጎ ነው የሚለውን መርህ እንዲጣስ በማድረግ፣ ፍርድ ቤቶች ነጻ እና ገለልተኛ የመሆን መርህ በማዛባት፣ ፍትሐዊ ችሎት እንዳይኖር በማድረግ፣ በሌሎች ተቋማት ኢፍትሐዊነትና ሙስና እንዲስፋፋ በማድረግ፣ በፍርድ ቤቶች ላይ የሕዝብ አመኔታ እንዳይኖር በማድረግ በአጠቃላይ የፍትሕ አስተዳደሩን በማዛባት ተጠያቂነት እንዳይኖር በማድረግ የሚያስከትለው አገራዊ ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ አክለውም የሙስና ውግያ ቀላል ውጊያ ስላልሆነ በጥንቃቄ መዋጋት እንደሚያስፈልግና በሙስና ላይ መፎከር ሳይሆን ጸንቶ በመቆም በጥንቃቄ መከላከል፣ በፍላጻው እንዳይወጉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የፍርድ ቤቱ የሴቶችና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ አሌክሳንደር አዳም በአንድ ሃገር ውስጥ ሙስና፣ ስርዓት አልበኝነትና ወንጀል ከተንሰራፋ እንዲሁም ዜጎች የሃገርን ክብር፣ የወገንን ፍቅር የማያውቁ ከሆነና ራስ ወዳድነት ከነገሰ፤ ግለሰቦች ለሃገር ልማት ምንም ዓይነት ቦታ ስለማይኖራቸውና ሃላፊነት ስለማይሰማቸው ለሀገራቸው ዕድገት እንቅፋት መሆናቸው አይቀርም ብለዋል፡፡ በመጨረሻም የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሊዲያ ደምሴ በአሉን አስመልክተው መልዕክት ያስተላለፉትንና በፕሮግራሙ የታደሙትን ዳኞች፣የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞችን አመሰግነው ለመልካም ስነ ምግባር ግንባታና ለፀረ ሙስና ትግል ውጤታማነት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል። Previous Article በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ጋር ውይይት አደረጉ Next Article ሀገር አቀፍ የዳኝነትና የፍትህ አካላት የጋራ የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ Print 2116