ዓመታዊ የስራ ዕቅድና አፈጻጸም እንዲሁም የሰራተኞች ፕሮግራም ተካሄደ
/ Categories: News

ዓመታዊ የስራ ዕቅድና አፈጻጸም እንዲሁም የሰራተኞች ፕሮግራም ተካሄደ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ዘርፍ ሠራተኞች የተሳተፉበትና በፍርድ ቤቱ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የሀሳብ ልውውጥ የተደረገበት የውይይት መድረክ ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሔደ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር በፍርድ ቤቱ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች በተሰሩ ሥራዎች ድምር ውጤት የተገኘውን መልካም አፈጻጸም እንዴት ማስቀጠል እንደሚገባና እና የጎደሉትን ደግሞ እንዴት ማሳካት እንደሚቻል በቀጣይ ጊዜ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ሥራ ተሰርቶ ውጤት ተገኝቷል ሲባል የተሰራው ሥራ እንከን አልባ ነበረ ሊባል እንደማይቻል ጠቁመው የእለቱ መድረክ ፋይዳም በዓመቱ ውስጥ የሠራናቸውን ሥራዎች ተመልሰን የምናይበት፣ ለመልካም አፈጻጸሞች ምስጋና የምናቀርብበት እና ለጉደሉት ደግሞ የነበረውን ክፍተት እንዴት እንሙላው ብሎ ለመነጋገር ጥሩ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚወጡ መመሪያዎች አፈጻጸም ላይ የሚውሉበት እንዲሁም ከዚህ አኳያ ሥራ እና ሠራተኛ ተገናኝቶ ውጤት የሚታይበት ዓመት እንደሚሆን ጠቁመው ከዚህ አንጻር በሚቀጥለው ዓመት የተሻለ የሥራ አካባቢ ለውጥ እንደሚደረግና የሠራተኛውን ሕይወት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሥራዎችን እንሰራለን ብለን እናምናለን ብለዋል፡፡

በዚህ መድረክም ምን አሳካን፣ ምን ጎደለ፣ ከሠራተኛውና ከፍርድ ቤቱ ምን ይጠብቃል፣ ፍርድ ቤቱስ ከባለሙያዎች ምን ይጠብቃል በሚለው ላይ በዝርዝርና በግልጽ መወያየት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ፍርድ ቤቱን የተሻለ ለማድረግ እያንዳንዱ ባለሙያ የሚያደርገው አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ ተቋሙን የተሻለ ለማድረግ በግልጽ መነጋገር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በቅድሚያ በፍርድ ቤቱ ስትራቴጅክ ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት አማካኝነት በቀረበው የፍርድ ቤቱ የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የዳኝነት ነጻነት እና ገለልተኝነት አተገባበርን ለማረጋገጥ፣ የዳኝነት ግልጽነትና ተጠያቂነት ሥርዓት ለማጠናር፣ የሬጅስትራር አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነትን ለማሻሻል እና ሌሎች የተከናወኑ ሥራዎች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

ከመዛግብት አፈጻጸም አኳያም በበጀት ዓመቱ የአንድ መስኮት አገልግሎትን በማጠናከርና በሥነሥርዓት ሕጉ መሠረት በማስተናገድ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለ18,998 መዛግብት አገልግሎት መስጠት እንደተቻለ ተገልጿል፡፡ በፍርድ ቤቱ በዕቅድ ከተያዙ 20,421 መዛግብት መካከል ለ16,648 መዛግብት ዕልባት መስጠት እንደተቻለም ተጠቁሟል፡፡

በሪፖርቱ ላይ የፍርድ ቤቶች የአገልግሎቶችና አሠራሮች ተደራሽነት፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ አጋርነትና ድጋፍን ለማሳደግ፣ የሕዝብ ግንዛቤን እና ተሳትፎን ለማሳደግ፣ የመምራትን እና መፈጸም ብቃትን ለማጎልበት እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውጤታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ሥራዎችም በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

በተመሳሳይም በክትትልና ግምገማ አስፈላጊነት እና በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክትትልና ግምገማ ሪፖርት ሥርዓት ላይ እንዲሁም በበጀት ዓመቱ በድጋፍ ክትትልና ግምገማ መድረኮች የተለዩ ጥንካሬዎች፣ ድክመቶችና የትኩረት አቅጣጫዎች በስፋት ተዳስሰዋል፡፡

በፍርድ ቤቱ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድም በስትራቴጅያዊ ትኩረት መስክ ስር ከተያዙ 13 ግቦችና ዋና ዋና ተግባራት አንጻር የተዳሰሱ ሲሆን ስለአፈጻጸም ምዘና መርሆዎች እና አተገባበርም በዳይሬክቶሬቱ ባለሙያዎች ማብራሪያ ቀርቦ ሠራተኞች ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል፡፡

በመድረኩ ላይ ከተሳተፉ ሠራተኞች በቀረበው ሪፖርት እና ዕቅድ ላይ ለቀረቡ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በፍርድ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የፍርድ ቤቱን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በዲጂታል ዘዴ የተደገፈ ለማድረግ በፌደራል ፍርድ ቤቶች እየተሰሩ ስለሚገኙ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሥራዎች እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር ስለተከናወኑ ተግባራትም የፍርድ ቤቱ የኢኮቴ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ዳንኤል ወርቁ አማካኝነት ሰፊ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

ይህን ተከትሎም ከሠራተኞች ጋር በተደረገ አጠቃላይ ውይይት የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ቀርበው በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እና ም/ፕሬዚደንት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ባደረጉት ንግግር በፍርድ ቤቶች ሥራ ላይ እንዲውል የሚደረገው ቴክኖሎጂ የሰው ልጅን የማይተካ መሆኑን ጠቁመው ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሰራ ያለው የዲጂታል ዘዴ ሥራን በማዘመን ቀልጣፋና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት አጋዥ እንደሚሆን ገልጸው ሥራ ላይ የሚውለውን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የተደራሽነት ችግር ላለባቸውና እና አቅም ለሌላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች እገዛ የሚደረግበት አሠራር የታሰበበት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በማጠቃለያ ንግግራቸው በሚቀጥለው ዓመት የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ በርካታ መተግበሪያዎች ወደሥራ የሚገቡበት ዓመት መሆኑንና በሒደት ፍርድ ቤቶች ወረቀት አልባ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው ለቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑንና ለሚመጣው የአሠራር ለውጥም ሠራተኞች ራሳቸውን ዝግጅ ማድረግ እንደሚገባቸው አንስተዋል፡፡

በፍርድ ቤቱ እስካሁን ለተገኘው ውጤትና ወደፊትም ለሚመዘገበው ስኬት የፍርድ ቤቱ ሠራተኞች ሚና የማይተካ መሆኑን በመግለጽ ሁሉም ሰራተኛ ለሚያደርገው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ከፍርድ ቤቱ ሠራተኞች መካከል በመልካም ሥነምግባራቸውና በታታሪነታቸው ተመዝነው ብልጫ ላመጡ ሶስት ሠራተኞች እንዲሁም በፍርድ ቤቱ ለረዥም ዓመታት አገልግለው በጡረታ ለተሰናበቱ 13 ግለሰቦች የገንዘብ ሽልማት እና የምስክር ወረቀት በማበርከት የዕውቅናና የምስጋና መርሐ-ግብር ተከናውኖላቸዋል፡፡

Previous Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም ጽ/ቤት የአሰራር ስርዓት መመሪያ ላይ የቫሊዴሽን ወርክሾፕ ተካሄደ
Next Article በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የተመራ ልዑክ የሲዳማ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ፣የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤትን፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሀዋሳ ምድብ ችሎት ጎበኙ።
Print
392