ዜና መግለጫ
/ Categories: News

ዜና መግለጫ

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከነሐሴ 1-30 ባለው ጊዜ መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት መስጠታቸውን ይቀጥላሉ

በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀፅ 38(2) መሰረት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከነሐሴ 1 እስከ መስከረም 30 ባለው ጊዜ ዝግ እንደሚሆኑ ይደነግጋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ዳኞች ባላቸው የትርፍ ጊዜ አስቸኳይ የሆኑ ጉዳዮችን ብቻ ሊያስተናግዱ እንደሚገባም አዋጁ ያስቀምጣል፡፡ ዳኞች ዓመቱን ሙሉ እጅግ አድካሚ የሆነ የዳኝነት አግልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በዚህም አዎንታዊ የሆኑ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ ይህን ስራ ይበልጥ ለማስቀጠል፣ ወደ 2015 ዓ.ም የሚያልፉ መዝገቦችን ቁጥር ለመቀነስ፣ የበሰሉ መዝገቦችን እልባት ለመስጠት፣ እስረኛ ያለባቸውን መዝገቦች ቅድሚያ ሰጥቶ ለመስራት እንዲያስችል በዳኞች ፈቃደኝነት ላይ በመመስረት የፌዴራል ፍርድ ቤቶቹ ከነሐሴ 1-30/2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ መደበኛውን የዳኝነት አገልግሎት መስጠታቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች ያላቸውን የዕረፍት ጊዜ መስዋዕት በማድረግ መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ፍቃደኛ በመሆናቸው እያመሰገነ፣ ተገልጋዩም በዚህ አግባብ የፍርድ ቤቶቹን አገልግሎት ማግኘት የሚችል መሆኑን ያሳውቃል፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማለትም የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ፤ ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2014 ዓ.ም በሕገ-መንግስት እና በሕግ የተጣለባቸውን የዳኝነት አገልግሎቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በዚህም በ2014 ዓ.ም በ12 ወራት ውስጥ 209,317 የሚሆኑ መዛግብት በሶስቱም የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቀርበው 176,797 ለሚሆኑ ጉዳዮች እልባት ሰጥተዋል፡፡ ከሰኔ 2014 ወደ ሐምሌ 2014 የተላለፉ  32,520 መዛግብትም በመታየት ላይ ይገኛሉ፡፡

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አማካይ የማጥራት ዓቅም 103.7፣ የመጨናነቅ ሁኔታ 1.18 እንዲሁም የክምችት ምጣኔ 0.18 ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በ2014 ዓ.ም የ12 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ከዓለም አቀፍ የፍርድ ቤቶች ውጤታማነት መለኪያ መስፈርቶች አንጻር ሲታይ የውጤታማነት ደረጃው ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታል፡፡  

በበጀት ዓመቱ 300 የሚሆኑ መዝገቦች በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ስርዓት እልባት በማግኘታቸው ባለጉዳዮች በአጭር ጊዜ እና ሰላማዊ ግንኙነታቸውን አስጠብቀው አለመግባባታቸውን እንዲፈቱ ከማድረግ ባሻገር የመደበኛ ችሎቶች የመዝገብ ጫና እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡

በበጀት አመቱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያን መነሻ በማድረግ ጉዳዮች እንደየተናጥል ባህሪያቸው እና የጊዜ ገደባቸው እልባት እንዲሰጣቸው ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህም በሶስቱም ፍርድ ቤቶች በአማካይ 90 ከመቶ የሚሆኑ ጉዳዮች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡ የወንጀል ጉዳዮችን በተመለከተ እስረኛ ያለባቸው መዛግብት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እልባት እንዲያገኙ እየተሰራ ይገኛል፡፡

======== // ========

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም

Previous Article «ትልቁ የመሪዎች መለያ አውቃለሁ ባይነት ሳይሆን ለመማር ዝግጁ መሆን ነው»
Next Article ፍርድ ቤቱ ሐሰተኛ የቃለ-መሐላ አቤቱታ ያቀረቡ ባለጉዳይን በችሎት መድፈር እንዲቀጡ ወሰነ
Print
130

Documents to download