ዜና መግለጫ:- ፌዴራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ስለመሆናቸው
/ Categories: News

ዜና መግለጫ:- ፌዴራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ስለመሆናቸው

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በየዓመቱ ከነሐሴ 1 እስከ መስከረም 30 ድረስ ዝግ እንደሚሆኑ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 በአንቀጽ 38 ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቶች የዜጎች መብቶችን የሚያስከብሩ የፍትህ ተቋማት በመሆናቸው እና የፍርድ ቤት ውሳኔና ትዕዛዝ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ወቅታዊ ምላሽ መስጠት ያስችል ዘንድ ፍርድ ቤቶቹ በከፊል ዝግ ሆነው የሚቆዩ ይሆናል፡፡

በዚሁ መሰረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከነሓሴ 1/2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30/2014 ዓ.ም ድረስ በከፊል ዝግ ሆኖ የሚቆይ ሲሆን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶቹን ከውዝፍ መዛግብት ነጻ የማድረግ ጽኑ ዓላማቸውን እውን ለማድረግ በከፊል ዝግ የሚሆኑበትን ጊዜ በማራዘም ከነሐሴ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30/2014 ዓ.ም በከፊል ዝግ ይሆናሉ፡፡

ፍርድ ቤቶቹ በከፊል ዝግ ሆነው በሚቆዩባቸው ቀናት አስቸኳይና ጊዜ የማይሰጡ ከዜጎች መሰረታዊ መብቶችና ከሃገር ሰላምና ፀጥታ ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደ የጊዜ ቀጠሮ፣ የዋስትናና የዕግድ ጥያቄዎች፣ የመያዣና የብርበራ ትዕዛዞች፣ በተፋጠነ ስነ-ስርዓት የሚታዩ የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች እንዲሁም ከቤተሰብ፣ ከሕፃናት ቀለብና አስተዳደግ ጋር የተያያዙ አጣዳፊ መሰረታዊ ጉዳዮች፣ ይግባኝ የተባለበት ጉዳይ ከመታየቱ በፊት የተላለፈው የእስራት ቅጣት ጊዜ የሚያልቅ ወይም በአመክሮ ከእስር መፈታት ውጤት ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳዮች፣ እንዲሁም ሌሎች አስቸኳይነታቸው እና አጣዳፊነታቸው የታመነባቸው ጉዳዮች በተረኛ ችሎቶች የሚስተናገዱ መሆኑ ከፕሬዝደንት ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፍ/ቤቶች በከፊል ዝግ በሚሆኑበት ጊዜ በዳኞች መልካም ፈቃድ የእረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው ለምርመራ፣ ለብይንና ለውሳኔ በቀጠሮ ወደ 2014 ዓ.ም የተሻገሩ መዛግብትን የማጥራት ስራ እንደሚሰሩም ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሰረት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1494 ውዝፍ መዛግብት እልባት እንደሚያገኙ የተገለጸ ሲሆን ውጤቱም ለባለጉዳዮች በቀጠሯቸው ቀን የሚገለጽ መሆኑን የፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት አመልክቷል፡፡

በተገባደደው የፍርድ ቤቶች በጀት ዓመትም ሶስቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በድምሩ ለ171, 276 መዛግብት እልባት የሰጡ ሲሆን ከነዚህም መካከል በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 14,836 መዛግብት፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 28,465 መዛግብት እና በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 127,975 መዛግብት እልባት የተሰጣቸው ናቸው፡፡

Previous Article የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት የትውውቅና የቃለ መሐላ መርሐ-ግብር ተካሔደ
Next Article በፍ/ቤቶች የዳኝነት ነጻነትን፣ ገለልተኝነትን እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተገለጸ
Print
2343