የህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ ፍትህ ሚኒስትር በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የስራ ጉብኝት አደረጉ
/ Categories: News

የህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ ፍትህ ሚኒስትር በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የስራ ጉብኝት አደረጉ

የህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ ፍትህ ሚኒስትር ሚስ ሂ ሮንግ እንዲሁም በኢትዮጵያ የቻይና ሪፐብሊክ አምባሳደር የሆኑት ሚስተር ቺን ሃይ ከልዑክ ቡድኖቻቸው ጋር በመሆን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀን 6/6/2017 ዓ.ም በመገኘት የጋራ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረትና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን የስራ ጉብኝትና ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ፍርድ ቤት የህዝብ አመኔታን ያተረፈ ተቋም እንዲሆን የለውጥ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ በመግባት በርካታ የለውጥ ስራዎች የተከናወኑ መሆኑ ገልጸው ከነዚህም መካከል በቴክኖሎጂ የታገዘ የዳኝነት ስርዓት ለመዘርጋት የለሙ እንዲሁም በመልማት ላይ ያሉ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች መኖራቸውን በመጥቀስ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አክለውም የሁለቱን ሀገራት ስትራጂያዊ አጋርነት ከማጠናከር ባሻገር የቆዩትን ተሞክሮዎችና የልምድ ልውውጦችን በመቀመር ማቆየት አስፈላጊ መሆኑና ለዚህም ቻይና እያደረገች ላለው ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

የህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ ፍትህ ሚኒስትር ክብርት ሚስ ሂ ሮንግ በበኩላቸው የቻይና ሪፐብሊክ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የቆየ ስትራቴጂክ አጋርነት እንዳላቸው ገልጸው የውይይቱ ዓላማ ይህንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እና ለማጠናከር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በተለይም የሁለቱ ሃገራት ፍትህ ስርዓትን ከማጠናከር አኳያ ከፍርድ ቤትና የፍትህ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት እና ድጋፋቸውንም ለመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ያለማቸውን እንዲሁም በመልማት ላይ ያሉ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል ፡፡

Previous Article "ስነ ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልእኮ ስኬት" በሚል መሪ ቃል ለፌደራል ፍርድ ቤቶች መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ
Next Article የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ልዑክ ቡድን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ
Print
1164