የህጻናት ተስማሚ ፍትህ ሞጁል ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ
/ Categories: News

የህጻናት ተስማሚ ፍትህ ሞጁል ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከ UNICEF ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የህጻናት ተስማሚ ፍትህ ሞጁል ላይ ከተለያዩ ክልሎች እና ከፌደራል ፍ/ቤት ለተወጣጡ ዳኞች እና ባለሙያዎች ለሶስት ቀናት የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ሃላፊ ዳኛ ተክለሐይማኖት ዳኜ ጽ/ቤቱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ፍ/ቤቶች የህጻናትን የላቀ ጥቅም ለማስከበር ይረዳቸው ዘንድ ከሚሰሩ ስራዎች ውስጥ የዳኞችን እውቀት እና ብቃት ለማሳደግ ስልጠናዎችን መስጠት መሆኑን፣እነዚህ ስልጠናዎችን ወጥ እና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማስቻል የስልጠና ማኑዋል መዘጋጀቱን ጠቅሰው በዚህ ማኑዋል ላይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ዳኞች ስልጠና ለመስጠት የአሰልጣኞች ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የስልጠና ሞጁሉ አዳዲስ በህፃናት ፍትህ ዙሪያ ያሉ ሀሳቦችን የያዘ እና ጥቅል በመሆኑ ላለፉት ወራት ሞጁሉን በማዘጋጀት ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ከተመረጡ ባለሙያዎች ጋር ሲሰራ እንደቆየ እና በአሁን ሰአትም ሞጁሉ ተጠናቆ ቀጣይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ለማከናወን ለታሰቡ ስልጠናዎች አሰልጣኞች ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቅሰዋል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን የሆኑት ዶ/ር እመቤት ሙሉጌታ ፣ዶ/ር ዮናስ ቢርመታ እንዲሁም ጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ ደሳ ቡልቻ ናቸው፡፡

በስልጠናው ከትግራይ፣አማራ እንዲሁም ኦሮሚያ ክልል ጨምሮ ከፌደራል የተውጣጡ ዳኞች እና ባለሙያዎች ተካፍለዋል፡፡

Previous Article የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አስተዳደር ሰራተኞች የድልድል መመሪያ ላይ ለድልድልና ቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ አባላት ገለጻ ተደረገ
Next Article ለ45 ተከላካይ ጠበቆች 2ኛ ዙር የ6 ቀን አቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠት ተጀመረ
Print
1015