የሌሎችን  የሥነምግባር ችግር ከሚዳኘው የዳኝነት ተቋም የላቀ የሥነምግባር ደረጃ እንደሚጠበቅ ተጠቆመ
/ Categories: News

የሌሎችን  የሥነምግባር ችግር ከሚዳኘው የዳኝነት ተቋም የላቀ የሥነምግባር ደረጃ እንደሚጠበቅ ተጠቆመ

ሕብረተሰቡ ከዳኞች የሚጠብቀውን የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት መጀመሪያ ዳኞች በላቀ የሥነምግባር ደረጃ ላይ ሊገኙ እንደሚገባ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ብርሐነመስቀል ዋጋሪ ገለጹ፡፡

ከፌደራል ፍርድ ቤቶች ለተውጣጡ ዳኞች በፌዴራል ዳኞች ሥነምግባርና የዲሲፒሊን ክስ ሥነሥርዓት ደንብ ላይ ለሁለተኛ ዙር በፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት አስተባባሪነት የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ከመስከረም 14-15 ቀን 2014 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው ቲኬ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተሰጥቷል፡፡

ክቡር ፕሬዚደንቱ በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በፍርድ ቤቶች ከትናንት ይልቅ ዛሬ የዳኝነት ነጻነትና ተጠያቂነት አተገባበር እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመው ይህንም በፍ/ቤቶች ረዘም ያለ ቆይታ ያላቸው ዳኞች የሚገነዘቡት ነው ብለዋል፡፡

ክቡር ፕሬዚደንቱ አክለውም የዳኘችን ነጻነትን ለማረጋገጥ የተሰራውን ያህል ተጠያቂነትን እውን ለማድረግ ያለመሠራቱን ጠቁመው ለዚህም ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል አንዱ የቅደም ተከተል ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የቅደም ተከተል ጉዳይን አንስተው ሲገልጹም የዳኝነት ነጻነትና ተጠያቂነት ተነጣጥለው የማይታዩ መርሆዎች ቢሆኑም መጀመሪያ ዳኞች ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ ሁኔታዎች መመቻቸት ያለባቸው በመሆኑ ለዚህ ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፌዴራል ዳኞች ሥነምግባርና የዲሲፒሊን ክስ ሥነሥርዓት ደንብ ላይ የተዘጋጀውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የሰጡት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ተክሊት ይመስል ሲሆኑ "የዳኞች ሥነምግባር ምንነት መሠረታዊ መርሆዎች እና የሚያስከትለው ተጠያቂነት" በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው ዓላማ በፌደራል ዳኞች የሥነምግባርና የዲሲፕሊን ክስ ሥነሥርዓት ላይ ለዳኞች የእርስ በእርስ መማማሪያ መድረክ በመፍጠር ዳኞች በሥነምግባር ምንነትና አስፈላጊነት ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲይዙ፣ የዳኝነት ሥነምግባርን ባህሪያት እንዲለዩ እና በዳኝነት ሥነምግባር መርሆዎችና ተነጻጻሪ ግዴታዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ለማድረግ ነው፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው በተጨማሪም የሥነምግባር ጥሰት ተጠያቂነት መሰረቶችን ለመለየት እንዲሁም በሥነምግባር ጉድለትና በፍርድ ሥራ ስሕተት መካከል ያለውን ብዥታ በውይይት ለማጥራት እንዲረዳ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው በቡድን ውይይት ጭምር ታግዞ ቀረበ ሲሆን በደንቡ ይዘት ላይ ከሶስቱም የፌደራል ፍርድ ቤቶች የተሳተፉ ዳኞች የሚፈለገውን ግንዛቤ የጨበጡበት እንደነበር ታውቋል፡፡

የፌደራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/2013 እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 ሥራ ላይ መዋላቸውን ተከትሎ ከዚህ በፊት ይሠራበት የነበረውን የፌደራል ዳኞች የሥነምግባርና የዲሲፒሊን ክስ ሥነሥርዓት ደንብ ቁጥር 1/2013 ድንጋጌዎች ከእነዚህ አዋጆች ጋር ለማጣጣም የተሻሻለው የፌደራል ዳኞች የሥነምግባርና የዲሲፒሊን ክስ ሥነሥርዓት ደንብ ቁጥር 3/2014 በፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጸድቆ ከሚያዚያ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article የፍርድ ቤቱ ሠራተኞች ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን አከበሩ
Next Article ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ግዥን በዕውቀት ሊመሩት ይገባል ተባለ
Print
50