Sunday, December 12, 2021 / Categories: News የሙስና ወንጀልን በትብብርና በአንድነት መንፈስ መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የፕሬዚደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቦጃ ታደሰ የሙስና ወንጀልን በትብብርና በአንድነት መንፈስ መከላከል እንደሚገባ ገለጹ፡፡ አቶ ቦጃ ታደሰ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በዓል አከባበርን አስመልክቶ በተዘጋጀ የገንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መድረክ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ሙስና ሕዝብ በመንግሥት እና በሕግ የበላይነት ላይ አመኔታ እንዲያጣ የማድረግ ጉልበት ያለው መሆኑን በመጥቀስ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በእጅጉ በማዳከምና በመጉዳት የሞራልና የሥነምግባር ቀውስ እንዲፈጠር የሚያደርገውን የሙስና ወንጀል በትብብርና በአንድነት መንፈስ መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት ከሚሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ የሙስና ጉዳዮች መሆናቸውን የጠቀሱት የፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ቦጃ ታደሰ፣ ፍርድ ቤቶች ሕግን መሰረት አድርገው በሚሰጡት ዳኝነት የተቋማት የአሠራር ሥርዓት ከሙስና የፀዳ እንዲሆን በማድረግ እና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ የሚጠበቅባቸውን በማከናወን ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም የፍ/ቤቱ ማሕበረሰብ በሙሉ አድሎአዊ አሠራርና ሙስናን መሠረት ያደረገ አስተሳሰብ እና ተግባርን በመዋጋት ፍርድ ቤት የዜጎች ዳኝነት አገልግሎት ማግኛ ብቸኛ ተቋም መሆኑን በመረዳት የፍርድ ቤቱ ዝና እና ስብዕና ይበልጥ ከፍ እንዲል ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በመድረኩ ላይ በፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሥነምግባር ዲቪዥን የሥልጠና ባለሙያ የሆኑት አቶ ሲሳይ ጌትነት ለፍ/ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ በሙስና መከላከልና በሥነምግባር ግንባታ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ የሥልጠና ባለሙያው የሰጡት ሥልጠና በሙስና ልዩ ባሕርያት፣ ሙስና በሚያስከትላቸው ጉዳቶች፣ ሙስናን ለመከላከል ከፍ/ቤቱ ስለሚጠበቁ ጉዳዮች እንዲሁም ሙስናን ለመከላከል የሥነምግባር መከታተያ ክፍሉ፣ አመራሩ እና ሰራተኞች ባላቸው ሚና ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናውን ተከትሎ በተደረገው አጠቃላይ ውይይት በፍ/ቤቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የሙስና እና ኢ-ሥነምግባራዊ ድርጊቶችን ለመከላከል በፍ/ቤቱ አመራር በኩል እየተዘረጉ ስለሚገኙ የሙስና መከላከያ የአሠራር ሥርዓቶች ከመድረክ ገለጻ ተደርጓል፡፡ ተሳታፊዎቹ ላቀረቧቸው የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ፣ በአገራችን ደግሞ «በሥነምግባር የታነጸ አመራር፣ ከሙስና ለፀዳች ኢትዮጵያ» በሚል መሪ-ቃል ለ17ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተገኙበት ታህሳስ 2 ቀን 2014 ዓ.ም በፍ/ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article ፍርድ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሴቶችና ሕጻናት ሥርዓተ-ችሎት እንዲዘጋጅ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቆመ Next Article ፍርድ ቤቱ በስትራቴጂያዊ እና ዓመታዊ ዕቅዱ ላይ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ማብራሪያ ሰጠ Print 1294