Wednesday, October 2, 2024 / Categories: News የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ልዑክ ቡድን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የልምድ ልውውጥ አደረገ፡፡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን እና የስራ ሃላፊዎችን ያካተተ ልዑክ ቡድን በቀን 21/01/17 ዓ.ም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የልምድ ልውውጥ አድርጓል፡፡ በልምድ ልውውጥ መድረኩ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ባደረጉት ንግግር በፍርድ ቤቶች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችና ያሉ ጉድለቶችን ለማረም የተጀመሩ ስራዎች በፌደራልም ሆነ በክልል ፍርድ ቤቶች ለየት ባለ እና በተቀነናጀ መልኩ ለማስኬድ እየተሞከረ መሆኑን ገልጸው እነዚህ ስራዎች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አክለውም የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ዝግጅት፣ የአሰራር ስርዓት የመዘርጋት እንዲሁም የተገልጋይን እርካታና የፍርድ ቤቶችን ውጤታማነትን የሚቀንሱ እንቅፋቶችን የማረም ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ተገማችና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የማስቻል ስራ ከቴክኖሎጂው ጎን ለጎን ትኩረት ተሰጥቶት በሁሉም የሃገሪቱ ፍርድ ቤቶች ላይ እንዲውሉ በማድረግ ቀልጣፋ የዳኝነት ስርአት መዘርጋትም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ኤርስኖ አቡሬ በበኩላቸው በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን በተመለከተ መልካም ተሞክሮ በመውሰድ ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን አንስተው ይህ እና መሰል መድረኮችም የፍትህ ስርዐቱን የተሻለ ለማድረግ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡ የተቋሙን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች እና ሌሎች የሪፎርም ስራዎች ላይም ገለጻና ውይይት የተደረገ ሲሆን የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የስራ ክፍል ሃላፊዎች ከፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት አቻዎቻቸው ጋርም የውይይት እና ልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡ ልዑክ ቡድኑ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትግበራ እና በመልማት ላይ የሚገኙትን የቴክኖሎጂ መሠረተልማቶች የጎበኙ ሲሆን በተለይም የስማርት ኮርት ሩም አገልግሎት አሰጣጥን፣ የዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ መሠረተ ልማት ዳታ ሴንተር እና ኔትዎርክ ኮንትሮል ሩሞችን ተመልክተዋል፡፡ Previous Article የአሜሪካ ኤምባሲ የዓለም አቀፍ ናርኮቲክስ እና የሕግ ተፈጻሚነት ቢሮ ልኡክ ከፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ጋር የአጋርነት ውይይት አካሄደ Next Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2017 ዓ.ም መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት በይፋ ተጀምሯል Print 195