የሰበር ሰርዓትን ማጠናከር ለዳኝነት ሪፎርም በሚል የቀረበ ጽሁፍ ላይ ውይይት ተደረገ
/ Categories: News

የሰበር ሰርዓትን ማጠናከር ለዳኝነት ሪፎርም በሚል የቀረበ ጽሁፍ ላይ ውይይት ተደረገ

የሰበር ሰርዓትን ማጠናከር ለዳኝነት ሪፎርም(Strengthening the cassation system for effective judicial reform) በሚል የቀረበ ጽሁፍ ላይ በቀን 27/11/2017 ዓ.ም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ አመራሮችና ዳኞች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡

ጽሁፉን ያቀረቡት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ክቡር ዳኛ ተፈሪ ገብሩ(ዶ/ር) እና ክቡር ዳኛ ቀነዓ ቂጣታ በአገሪቱ ወጥ የሆነ የህግ አተረጓጎም እንዲኖር፣ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ አስቀድሞ የወጡ ውሳኔዎችን ለይቶ በማውጣት ወጥ ወደሆነ የውሳኔ አሰጣጥ የሚመጣበት መንገድ፣ የሰበር ውጤታማነት ከህገመንግስቱ፣ ከመሰረታዊ መብቶችና የህግ ልዕልና ከመጠበቅ እና ከማስጠበቅ አንጻር ምን መምሰል እንዳለበት አብራርተዋል።

በቀረበው ጽሁፍ ላይ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እና የፌደራልና የክልል የህግ ማዕቀፎች የተዳሰሱ ሲሆን የፌደራል ሰበር ችሎት በህገመንግስቱም ሆነ በዝርዝር ሕጉ የተጣለበትን ሃላፊነትና ግዴታ እንዲወጣና የተቋቋመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የሰበር አጣሪም ሆነ የሰበር ችሎቶች በአዋጅ ቁጥር 1234/13 የተቀመጡትን የፈቃደ ስልጣን ለማጥበብ፣ ግልጽነትን ለማስፈን፣ ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የሰበር አለማን ለማሳካት እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን መስፈርቶቹን በጥብቅ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል፡፡

ለሰበር የሚቀርቡ ጉዳዮች የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የተፈጸመ የህግ ስህተት ወይም በፍርዱ ይዘትና ሂደት የፍትህ መጓደልና የመብት ጥሰት መፈጸሙን የሚያመላክት ሆኖ የፍርዱን ይዘት፣ ውጤት ወይም ድምዳሜ የማሻሻል፣ የመለወጥ ወይም የመሻር ውጤትን የሚያስከትል እንደመሆኑ መጠን ፍርድ ቤቶች ህግን የመተርጎም ስልጣናቸውን የሚፈለገውን ግብ እንዲመታ የዳኝነት ሪፎርሙ በእቅድና ስትራቴጂ በማስደገፍ የማይተካ የህግ የበላይነትን ማስከበር ሚናቸውን ማስቀጠል አለባቸው ተብሏል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የሰበር ውሳኔዎች በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች አስገዳጅነት ያላቸው ውሳኔዎች እንደመሆናቸው አጠቃላይ የፍትህ ስርአት ላይ ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቶች በእጃቸው ባለ ነገር ላይ መምከርና የሰበር አሰራር ከተዘረጋበት አላማ አንጻር በየግዜው በመፈተሽ፣ያስገኘውን ውጤት በመለካት፣ የመጣውንም ውጤት ከውሳኔዎች ተገማጭነት እና ጥራት አንጻር በመመዘን ዋነኛ የፍርድ ቤቶች የሪፎርም አካል ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

አክለውም ከውስጥ የሚመጣ ለውጥ ረጅም ጉዞ የሚሄድ በመሆኑ ዳኞች በጋራ በመምከር የመፍትሄ አካል ሲሆኑ የውሳኔ አሰጣጡ ተገማች፣ ወጥ፣ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ እና ጥራት ያለው እንዲሆን ያግዛል ብለዋል፡፡ በ2018 በጀት ዓመትም የዳኝነት ስራው ላይ የሚያተኩሩ ስራዎች ላይ በሰፊው የሚሰራበት ከመሆን ባለፈ የሚቃረኑ የውሳኔ ሀሳቦች ተመርጠው ጥናት የተደረገበት ሰነድ ላይ እና ተያያዥነት ያላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች የሚደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መድረኩ የተዘጋጀው በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ( UNDP Ethiopia ) ድጋፍ ነው፡፡

Previous Article ለኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማሕበር ጽ/ቤት የሰበር ውሳኔዎች የድምጽ ቅጂ ተበረከተ
Next Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 ዓ.ም አመታዊ የስራ አፈጻጸም የግምገማና የውይይት መድረክ ተካሄደ
Print
783