የስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት አማካሪ ድርጅት ዕቅድ ዝግጅቱ ያለበትን የስራ ደረጃ ለዐብይ ኮሚቴው ገለጸ
/ Categories: News

የስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት አማካሪ ድርጅት ዕቅድ ዝግጅቱ ያለበትን የስራ ደረጃ ለዐብይ ኮሚቴው ገለጸ

የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን 3ኛ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ለማዘጋጀት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተቀጠረው ጥምር አማካሪ ድርጅት በጽንሰ ጥናት ሪፖርቱ ባስቀመጠው የድርጊት መርሃ ግብር መሰረት የዕቅድ ዝግጅት ስራው ያለበትን ደረጃ በፍርድ ቤቱ በኩል ስራውን እንዲከታተልና አስፈላጊ ግብአቶችን እንዲያቀርብ ሃላፊነት ለተሰጣቸው ዐብይ እና ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ዛሬ ሚያዚያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ገለጸ፡፡

አማካሪ ድርጅቱ በጽንሰ ጥናት ሪፖርቱ በደረጃ ሁለት ከተጠቀሱ ለስትራቴጂያዊ ዕቅድ ዝግጅት መነሻ የሆኑ ሰትራቴጂያዊ ትንተና ስራዎች መካከል የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ወቅታዊ ሁኔታ ትንተና እና ጠንካራና ደካማ፣ አስቻይና የስጋት ሁኔተዎችን የመተንተን ስራ እያከናወነ መሆኑን ባቀረበው ሪፖርት ገለጿል፡፡  ለዚህም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ መረጃ የማሰባሰብ ስራ ከሞላ ጎደል ማገባደዱን ያመለከተ ሲሆን የተገኙትን መረጃዎች የማደራጀትና የመተንተን ስራ ጎን ለጎን እየተሰራ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ እንዲሰበሰብ ቀደም ብለው ከተለዩ አካላት መካከል መረጃ የተሰበሰበባቸውን እና በሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮችን በዝርዝር እንዲያቀርብ በዐብይ ኮሚቴው  ዕድል የተሰጠው አማካሪ ድርጅቱ የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ የመሰብሰብ ስራ ዋናው ፈታኝና አድካሚ ስራ መሆኑን ጠቅሶ ከፍርድ ቤት አመራሮች፤ ከዳኞች፤ ከልዩ ልዩ ክፍል ሃላፊዎች፤ ከክልል ፍርድ ቤቶች (አማራ ኦሮሚያ እና ደቡብ)፤ ከአቃቤ ህግ፤ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ከህግ ባለሙያዎችና ማህበሮቻቸው፤ ከልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ማህበራት እና ከመሳሰሉት መረጃ ለመሰብሰብ ጥረት ተደርጓል፡፡  ከነዚህም መካከል 95 በመቶ ከሚሆኑት በቃለመጠይቅ እና በውይይት በቂ መረጃ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡ 

በወቅታዊ እና አስቸኳይ ስራዎች ምክንያት የቀሩትን የመረጃ ምጮች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት ማግኘት አለመቻሉን ተናግረው የመረጃ ምጮቹን በሌላ ቀጠሮ ለማግኘት ጥረት እያድረግን ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የሁለተኛ ደረጃ መረጃ የሚሰበሰብባቸው የመረጃ ምንጮች ዓለም አቀፍ የህግና የመርህ ሰነዶች፤ ሃገራዊ ህጎች፤ ሪፖርቶች፣ እቅዶች፣ እና ተጨማሪ የውጭ ሃገራት መልካም ተሞክሮዎች መሰብሰባቸውን አማካሪ ድርጅቱ ባቀረበው ሪፖርት አብራርቷል፡፡  

የዐቢይ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው የፍርድ ቤቶች ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን ለመለየት የመጀመሪያ ደረጃ ከሚሰበሰብባቸው የመረጃ ምንጮች መካከል ተከላካይ ጠበቆች፣ ፍርድ አፈጻጸም፣ በጠበቃ ያልተወከሉ ባለጉዳዮች እና የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲካተቱ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም ዐብይ ኮሚቴው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የቀጣዩ አምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ከሐምሌ 2013 ዓ.ም ጀምሮ መተግበር ያለበት በመሆኑ የዕቅዱን ረቂቅ በባለድርሻ አከላት የማስተቸት እና ተጨማሪ ግብአት የማሰባሰብ፤ የማዳበር እና በአመራሩ የመስጸደቅ፤ ለፍርድ ቤቱ ማህበረሰብ የማስተዋወቅ፤ የማስረጽ ስራዎች ከሰኔ በፊት ማለቅ እንዳለበት አሳስቦ አማካሪ ድርጅቱ ያወጠውን መርሃ ግብሩን ጠብቆ ጥራት ያለው፤ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል እና ፍርድ ቤቱን በአፈጻጸምና በአገልግሎት አሰጣጥ የሚያሳድግ ዕቅድ እንዲያዘጋጅ አጽንኦት ሰጥቶ መክሯል፡፡

በዚህም መሰረት አማካሪ ድርጅቱ መረጃ ማደራጀትና መተንተን ስራ ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ እና መረጃ መሰብሰብ ተጨማሪ ጊዜ የወሰደ በመሆኑ አነስተኛ የመርሃ ግብር ማስተካከያ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርቦ በዐብይ ኮሚቴው ተቀባይነት አግኝቷል፡፡      

አማካሪ ድርጅቱ የፍርድ ቤቶች ስልጣንና ተግባራት ትንተና እና የቀድሞ ስትራቴጂያዊ ዕቅዶች ዝግጅትና አፈጸጸም አጭር የግምገማ ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ 

አድቫንስ አሶሺየትስ እና አፕፍሮንት አማካሪ ድርጅቶች የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን 3ኛው (ከ2014-2018 ዓ.ም) ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ለማዘጋጀት የተቀጠሩ ጥምር አማካሪ ድርጅቶች ሲሆኑ ሳይንሳዊ እና ከፍርድ ቤት መሰረታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ባህሪ ጋር የተጣጣመ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ለማቅረብ በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article በጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫ ጉዳዮችን እንዲመለከቱ ለተደራጁ ልዩ ችሎቶች የስራ አቅጣጫ ተሰጠ
Next Article የፌዴራል ፍ/ቤቶች ከፍተኛ አመራር እንዲያጸድቅ በቀረቡለት ሁለት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ተወያየ
Print
388