የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን መሰረት አድርጎ በሚቋቋም ልዩ ችሎት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲካሄድ የቆየው የምክክር መድረክ ተጠናቋል
/ Categories: News

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን መሰረት አድርጎ በሚቋቋም ልዩ ችሎት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲካሄድ የቆየው የምክክር መድረክ ተጠናቋል

ከፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት እና ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች፣ እንዲሁም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉበት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን መሰረት አድርጎ በሚቋቋም ልዩ ችሎት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከቀን 29/02/2017 እስከ 30/02/2017 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የቆየው የውይይት መድረክ ተጠናቋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ በኢትዮጵያ በተለያየ ግዜ በተፈጠሩ አለመግባባቶች የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በንብረትና የሰው ህይወት ላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑን ጠቅሰው አኝህን ችግሮች ለመፍታት ከእውነት ማፈላለግ፣ከካሳ፣ ከእርቅ ፣ እንዲሁም ምህረት ከማድረግና ጉልህ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ተሳትፎ ያላቸውን ሰዎች የወንጀል ተጠያቂነት ከማስከተል አንጻር የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው መቀረጹንና ለትግበራውም የተለያዩ አካላት ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን አንስተው ከእነዚህም መካከል ፍርድ ቤቶች ከወንጀል ተጠያቂነት ጋር በተያያዘ ልዩ ችሎት የማደራጀት ሃላፊነት የተሰጣቸው በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ ህገመንግስቱንና የሽግግር ፍትህ ፖሊሲውን መሰረት አድርጎ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

አክለውም ዳኞች በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሰጧቸው ሀሳብ አስተያየቶች እንደ ግብዓት የሚወሰዱና ቀጣይ ውይይቶችም የሚደረጉበት እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡ በመጨረሻም የአርቃቂ ኮሚቴ አባላት ላደረጉት አስተዋጽኦ፣ ተሳታፊ ዳኞች ላደረጉት የላቀ ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ ሽግግር ፍትህ ፖሊሲን እንዲሁም የልዩ ችሎት ማቋቋሚያ አዋጁን በተመለከተ ገለጻ፣ ውይይት እና የግብዓት ማሰባሰብ፣ የህግ ማዕቀፎች ላይም ሰፊ ዳሰሳ ተደርጓል፡፡

መድረኩ የተዘጋጀው በዩ.ኤን.ዲ.ፒ (UNDP) ድጋፍ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስተባባሪነት ነው፡፡

Previous Article የቻይና ናሽናል የዳኞች ኮሌጅ ልዑካን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ
Next Article በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ላይ ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ረዳት ዳኞች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ
Print
377