የተማሪዎችን የሕግ ግንዛቤ ለማሳደግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
/ Categories: News

የተማሪዎችን የሕግ ግንዛቤ ለማሳደግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ያላቸውን የሕግ ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በትምሕርት ሚኒስቴር፣ በሳይንስና ከፍተኛ ትምሕርት ሚኒስቴር እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መካከል ተፈረመ፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ የተፈረመው ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በተካሔደ መድረክ ላይ ሲሆን በተለያዩ ርዕሶች ላይ የፓናል ውይይትም ተካሒዷል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ በመድረኩ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የተማሪዎች የሕግ ግንዛቤ ማሳደጊያ መርሐ-ግብር ባለፉት ሶስት ዓመታት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ሲሆን የቆየው የማሻሻያ መርሐ-ግብር (Reform) አካል የሆነና የሕዝብን የሕግ ግንዛቤ ለማሳደግ የተያዘ ዋና ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአራቱ መንግሥታዊ ተቋማት በጋራ የሚተገበረው የተማሪዎች የሕግ ግንዛቤ መርሐ-ግብር ዝርዝር የድርጊት መርሐ-ግብር የተዘጋጀለት መሆኑን የጠቀሱት ክብርት ፕሬዜዳንትዋ የሚከናወኑ ተግባራትም የፍትሕ ክበባትን በትምሕርት ቤቶች በማቋቋም ተማሪዎች በክበባት በኩል በተለያዩ የሕግ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም ለሕግና የሕዝብ አስተዳደር ተማሪዎች በፍ/ቤቶች የኢንተርንሽፕ ፕሮግራም እና የምስለ ችሎት ውድድሮችን ማዘጋጀትን እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡

የተማሪዎች የሕግ ግንዛቤ የድርጊት መርሐ-ግብሩ የተማሪዎችና የዳኞች የውይይት መድረክ ማዘጋጀትን፣ ሕግና ፍትሕን በኪነ-ጥበብ ውጤቶች የመግለጽ ውድድሮች ማካሔድን በተጨማሪም የሴት የሕግ ትምሕርት ቤት ተማሪዎች የሜንተርሽፕ ፕሮግራም መተግበርን እንደሚያካትት ጠቁመዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነት የፊርማ ሥነሥርዓቱን ተከትሎ ወጣቶች የሰብአዊ መብቶችን በማስከበር ውስጥ ባላቸው ድርሻ ላይ፣ ወጣቶችና የወንጀል ሕግ ሁኔታዎች በተለይም ከአደንዛዥ ዕጽ አጠቃቀም አንጻር የተዳሰሰበት እንዲሁም የሕግ ምሩቃንን ለተግባራዊ ሥራ ዝግጁ ማድረግን በተመለከተ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ወጣቶች በሰብአዊ መብቶች አከባበር ሥርዓት ውስጥ ስላላቸው ሚና ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የንቃተ ሕግ ትምሕርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ እንዳልካቸው ወርቁ፣ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀሎችና አደገኛ ዕጽ ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር አበራ ቡሌና እንዲሁም በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ፕሮግራም አማካሪ አቶ በብዙህ ሙሉጌታ በወጣቶችና የወንጀል ሕግ ሁኔታዎች እንዲሁም በአደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚነት ላይ ከተለያየ ዕይታ አንጻር ገለጻ አድርገዋል፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት ዲን እና ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሰለሞን ንጉሴ የሕግ ምሩቃንን ለተግባራዊ ሥራ ማብቃት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

በባለሙያዎች የቀረቡትን ማብራሪያዎች ተከትሎ ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው በፓናል ውይይቱ አቅራቢዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት፣ ከሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማሕበር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የተጋበዙ ተሳታፊዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልዩ ልዩ የመንግስትና የግል ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተጋበዙ ተማሪዎችም ተገኝተዋል፡፡

Previous Article ለስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት የተካሄዱ የትንተና ጥናቶች ላይ ዓብይና የቴክኒክ ኮሚቴ ተጨማሪ ግብአት ሰጡ
Next Article ፍርድ ቤቱ ባቀረበው የበጀት ጥያቄ ላይ በምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጠ
Print
3788