Wednesday, August 27, 2025 / Categories: News የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ወጣ የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 በመጽሐፍ መልክ መታተሙን ተከትሎ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ ክቡራን ዳኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነሐሴ 20 ቀን 2017 ዓ.ም የእውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም መጽደቁን ጠቁመው ተፈጻሚ መሆን የጀመረውም ከሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መመሪያው መሠረታዊውን የቅጣት ግለሰባዊ መርህ የሚቀበል እና የቅጣት መወሰኛ ቀመር የሚያስቀምጥ በመሆኑ ውሳኔዎች ተገማች እና ወጥ እንዲሆኑ እንደሚያስችል ጠቁመው ይህም በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ ወንጀሎች ተመሳሳይና ተቀራራቢ የቅጣት ውሳኔዎች እንዲሰጡ በማድረግ የፍርድ ቤቶችን ተዓማኒነት እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 ይዞ ከመጣቸው ዘርፈ ብዙ ለውጦች መካከል ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ ከነበረው መመሪያ ውስጥ ተካተው ከነበሩት ወንጀሎች በተጨማሪ ለሌሎችም ተጨማሪ ወንጀሎች ደረጃና እርከን እንዲወጣላቸው መደረጉ ተጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩልም የወንጀል ደረጃዎች እንዲጨመርባቸው የተደረጉ ወንጀሎች ያሉ ሲሆን የገንዘብ መቀጮ አስተማሪ ለማድረግም ይህን በሚመለከት የእርከን ሰንጠረዥ ላይ ማሻሻያ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡ በመድረኩ ላይ የቅጣት አወሳሰን መመሪያውን የማሻሻል ሂደቶች እና የመመሪያው ይዘትን በተመለከተ የመመሪያ ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩት በክቡር አቶ ተክሊት ይመስል እና የመመሪያ ዝግጅት ኮሚቴ አባል በሆኑት አቶ በብዙህ ሙሉጌታ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ በሥነሥርዓቱ ላይ በቅጣት አወሳሰን መመሪያው ዝግጅት ለተሳተፉ የመመሪያ ዝግጅት ኮሚቴ አባላት እንዲሁም መመሪያው ከዝግጅት ጀምሮ ለሕትመት እስኪበቃ ድረስ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ላደረገው የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ እና የወንጀል ፍትሕ ስርአት ማሻሻያ ፕሮጀክት የቴክኒክ ድጋፍ ክፍል የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡ Previous Article የፌደራል እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ውዝፍ መዛግብትን ለማጥራት የሚያግዝ የመግባቢያ ስምምነት ከጀስቲስ ፎር ኦል-ፕሪዝን ፌሎውሽፕ ኢትዮጵያ ጋር ተፈራረሙ Next Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንጻ ግንባታ ያለበት ደረጃ ተገመገመ Print 608