Wednesday, May 21, 2025 / Categories: News የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ክልላዊ ዳይሬክተር (The office of the United Nations High Commissioner for Human Rights (OHCHR) regional director) ሚስተር ማርሴል አክፖቮ የተመራ ልዑክ ቡድን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ክልላዊ ዳይሬክተር (The office of the United Nations High Commissioner for Human Rights (OHCHR) regional director) ሚስተር ማርሴል አክፖቮ እና ልዑክ ቡድናቸው በቀን 12/09/2017 ዓ.ም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ውይይት እና የስራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ልዑክ ቡድኑ በነበረው ቆይታ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ተግባራት በተለይም በቴክኖሎጂ የታገዘ የዳኝነት አገልግሎት ከመስጠት አንጻር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ላይ በሰፊው ተወያይተዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ፍርድ ቤቶች በቴክኖሎጂ በመታገዝ ቀልጣፋና ተደራሽ የሆነ የዳኝነት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራት ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያማከለ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ማድረግ እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ ሚስተር ማርሴል አክፖቮ በበኩላቸው ለአንድ ሀገር የፍትህ ስርዓት መጠናከር የዳኝነት አካሉ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ረገድ ፍርድ ቤቶችን በማዘመን ጉዳዮችን በተፋጠነ መንገድ መቋጨት እና ውጤታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል፡፡ ልዑክ ቡድኑ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚገኙ የስማርት ኮርት ሩሞችን የጎበኘ ሲሆን በቀጣይም የልምድ ልውውጥ መድረኮችን ለማመቻቸትና እገዛ ለማድረግ OHCHR ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ Previous Article ለፌደራል ፍርድ ቤቶች መካከለኛ አመራሮች እና ሰራተኞች ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተጠናቀቀ Next Article በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የለማ የኢፋይሊንግ፣ ኢሊቲጌሽንና ሰነድ ልውውጥ መተግበሪያ ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ተካሄደ Print 971