Tuesday, July 15, 2025 / Categories: News የተዘዋዋሪ እና ቋሚ ምድብ ችሎቶች ክትትል እና ግምገማን ዓላማ ያደረገ ጉብኝት ተካሔደ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንት በክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ የተመራ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመራሮች ልዑክ በሶማሌ እና በሐረሪ ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም በድሬዳዋ ምድብ ችሎቶች እና የከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች በመዘዋወር የክትትል እና ግምገማ ጉብኝት አካሄደዋል፡፡ አመራሩ የመጀመሪያ የስራ ጉብኝት ያደረገው የፌደራል ጉዳዮችን በውክልና የማየት ስልጣን ከተነሳባቸው ክልሎች አንዱ በሆነው በሶማሌ ክልል ሲሆን እስካሁን በነበረዉ አሰራር የፌዴራል ጉዳዮች የሆኑት ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ ችሎት ዳኞች በየጊዜ እየሄዱ የዳኝነት አገልግሎት ሲሰጡ የነበረ ሲሆን የአገልግሎት አሰጣጡ በሚሻሻልበት ጉዳይ ላይ ዉይይት ተደርጓል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንትን ጨምሮ የክልሉ ፍትህ አካላት ቢሮ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን የሶማሌ ክልል በቆዳ ስፋት ትልቅ በመሆኑ እና በክልሉ የሚታዩ የፌደራል ጉዳዮች በባህሪያቸዉ ዉስብስብ ስለሆኑ ዳኞች በቂ ጊዜ ወስደው ለጉዳዮች በጊዜ እልባት መስጠት እንዲችሉ ቢያንስ አንድ ችሎት በክልሉ መቋቋም እንዳለበት በውይይት መድረኩ ተነስቷል፡፡ በተጨማሪም በክልሉ የሚገኘዉ ማረሚያ ቤት ጠባብ በመሆኑ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዉሳኔ ያገኙ ታራሚዎች በሌሎች የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሄደዉ እንዲታረሙ የሚያደርግ አሰራር እንዲኖር የክልሉ ፍትህ አካላት የጠየቁ ሲሆን በተነሱ ጉዳዮች ላይ በክብርት ምክትል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ማብራሪያ እና አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ በዚሁም መሰረት በክልሉ ቋሚ ችሎት እንዲኖርና የዳኝነት አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል ሁኔታ ወደ ፊት ሊመቻች እንደሚገባ እንዲሁም ከማረሚያ ቤት ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጉዳይ በፌዴራል ደረጃ ያለዉ የፍትህ አካላት አብይ ኮሚቴ እንዲመክርበት እንዲደረግ ሀሳብ ቀርቧል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ሌሎች ቦታዎች ላይ የኢ-ፋሊንግ እና የቪዲዮ ኮንፍረንስ ማእከል እንዲገነባ ከስምምነት የተደረሰ ሲሆን የዳኝነት አገልግሎት በቴክኖሎጂ ታግዞ በርቀት ላይ ለሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎች አገልግሎት በሚሰጥበት አሰራር ላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አስተያየት ቀርቧል፡፡ በመጨረሻም የክልሉ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝዳንትን እና ሌሎች የፌደራል ፍርድ ቤቶችን አመራሮች ያነጋገሩ ሲሆን በወቅቱም ለማስቻያ ቦታ የሚሆን እና ለችሎቱ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት አንጻር ክልሉ በቂ ትብብር እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ በሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ተገኝቶ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢፋይሊንግ እና የቪዲዮ ኮንፍረንስ ማዕከል ያለበትን ሁኔታ የጎበኘ ሲሆን አገልግሎቱን የበለጠ ዉጤታማ ሊያደርግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሀረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤን ጨምሮ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮች ጋር ዉይይት ተካሂዷል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወሰዳቸዉን የቴክኖሎጂ ተሞክሮዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ተግባራዊ ማድረጉም በጉብኝቱ ወቅት የታየ ሲሆን በቀጣይነትም ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልል ፍርድ ቤቶችን ከማጠናከር አኳያ አጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ በውይይት መድረኩ የተነሳ ሲሆን ክብርት ም/ፕሬዝዳንትም የፌዴራል እና የክልል ፍርድ ቤቶች ግንኙነት ከዚህ በላይ ሊጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የድሬዳዋ ምድብ ችሎቶችንም የልዑካን ቡድኑ የጎበኘ ሲሆን የምድብ ችሎቶችን የማስቻያ ቦታ ከዚህ በበለጠ ሁኔታ ለአገልግሎት ምቹ ለማድረግ ሊሰራበት እንደሚገባ በአመራሩ ተገልጿል፡፡ ከሁለቱ የድሬዳዋ ምድብ ችሎቶች ዳኞች ጋር አመራሩ ውይይት በማድረግ ዳኞች ላነሷቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶችበ ክብርት ም/ፕሬዚዳንት ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ዳኞች በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ ከዚህ ከዚህ የበለጠ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ከስምምነት ተደርሷል፡፡ የልዑክ ቡድኑ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም በመገኘት ጉብኝት ያደረገ ሲሆን ፍርድ ቤቱ የስራ ቦታን ምቹ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እያከናወነ ያለዉን ሥራ አድንቀዋል፡፡ Previous Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳኞችና የስራ ኃላፊዎች የአረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ Next Article የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ወንጀል ችሎት ምድብ የሬጅስትራር አንድ መስኮት አገልግሎት ተመረቀ Print 751