Monday, November 17, 2025 / Categories: News የተግባር ልምምድ (ስልጠና) በዲጂታል የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች እየተሰጠ ይገኛል በዲጂታል የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከቀን 06-07/03/2018 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የሚቆይ የተግባር ልምምድ (ስልጠና) ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች እየተሰጠ ይገኛል። ስልጠናው በዋነኝነት ያተኮረው ከክስ መመስረት እስከ ውሳኔና የውሳኔ አፈጻጸም ድረስ ያለውን የዳኝነት ሂደት በቀጥታ(ኦንላይን) አገልግሎት የሚሰጡበትን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር(INSA) ጋር በመተባበር ያለማው ኢንቲግሬትድ ኬዝ ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም (ICMIS) ሲስተም ወደ ትግበራ ሲገባ የተሳካ እንዲሆንና ዳኞች ከሲስተሙ ጋር በፍጥነት ተዋውቀው የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው፡፡ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP Ethiopia) ተወካይ አቶ ፍስሃ መኮንን የፍርድ ቤቶችን አሰራር በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ በማድረግ ተአማኒነት ያለው አካል እንዲሆን ሁሉም ደረጃ ላይ ያሉ ፍርድ ቤቶች ዲጂታል አሰራርን የተላበሰ አሰራር ሊከተሉ እንደሚገባ እና ለዚህም የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP Ethiopia) መሰል ስልጠናዎች ላይ የገንዘብና አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት ለማዘመን በተጨባጭ እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራትና ያለውን ቁርጠንነት አድንቀዋል፡፡ በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ በዳኝነት አገልግሎት የፍርድ ቤቶች መዘመን ለላቀ የዳኝነት አገልግሎት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ አተገባበሩ ላይ የሁሉም ቁርጠኝነትና ርብርብ የሚፈልግ መሆኑን አንስተው ቴክኖሎጂውን ከማልማት ባለፈ የትግበራው ምእራፍ የታሰበለትን ግብ ይመታ ዘንድ ስራ ላይ እንዲውል የስራው ባለቤት የሆኑት ዳኞች፣ ሬጅስትራሮች፣ ረዳት ዳኞች እንዲሁም አጠቃላይ የፍርድ ቤት ማህበረሰብ ከቴክኖሎጂው ጋር በቅርበት በመተዋወቅ እና በመረዳት በቂ ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ አክለውም ቴክኖሎጂው ወደ ትግበራ ከመግባቱ በፊትም ሆነ ወደ ትግበራ ከገባ በኋላ ከሲስተሙ ጋር በደንብ መግባባት ላይ እስከሚደረስ ተመሳሳይ ልምምዶች እና ቀጣይነት ያላቸው የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንዲዘጋጁ ፍርድ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ የተግባር ልምምዱን በቡድን እገዛ የሚያደርጉ የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA)እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለሙያዎች ድጋፍ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ መድረኩ የተዘጋጀው በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP Ethiopia) የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡ Previous Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሪሶርስ ኢንሪቺንግ አፍሪካን ላይቭስ በሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት አስተባባሪነት የተሰበሰቡ መጽሃፍቶችን ተረከበ Next Article በአገልግሎት አሰጣጥና የደንበኞች አያያዝ ላይ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ Print 597