የቻይና ናሽናል የዳኞች ኮሌጅ ልዑካን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ
/ Categories: News

የቻይና ናሽናል የዳኞች ኮሌጅ ልዑካን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ

የቻይና ናሽናል የዳኞች ኮሌጅ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር እንዲሁም በኢትዮጵያ የቻይና ምክትል አምባሳደርን ያካተተ የልዑክ ቡድን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀን 19/02/2017 ዓ.ም በመገኘት ጉብኝት አድርገዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የቻይና ናሽናል የዳኞች ኮሌጅ ከዚህ ቀደም በቻይና ለፌደራል ዳኞች ላዘጋጀው የስልጠናና የጉብኝት መርሃ ግብር ምስጋና አቅርበው የልዑክ ቡድኑ የዳበረ ልምዱን ለማካፈል እና ተቋሙን ለመጎብኘት ኢትዮጵያ ድረስ መምጣቱ በፍ/ቤቱ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ለማጠናከርና የሁለቱን ሀገራት ትብብር ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የቻይና ናሽናል የዳኞች ኮሌጅ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዋንግ ዚያኦፋንግ በበኩላቸው ጉብኝቱ በቀጣይ በትብብር ለመስራትና የዳኞችን አቅም ከማሳደግ አንጻር የተሸለ እድል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ልዑካን ቡድኑ በቆይታቸውም የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች መዋቅር እና የዳኝነት ስርአት፣ እየተሰሩ ያሉ የለውጥ ተግባራት እንዲሁም በዳኞች ስልጠና ዙሪያ ሰፊ ገለጻ የተደረገላቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱ ያስገነባውን የስማርት ኮርት ሩሞችና የዋይድ ኤሪያ ዳታ ሴንተርንም ጎብኝተዋል፡፡

የቻይና ናሽናል የዳኞች ኮሌጅ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዋንግ ዚያኦፋንግ በተጨማሪም ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እና ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ በነበራቸው የተናጠል ውይይት በቀጣይ ተቋማቱ በትብብር ስለሚሰሯቸው ስራዎች እንዲሁም የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ተወያይተዋል፡፡

ልዑክ ቡድኑ በቀጣይ ቀናትም የፌደራል ከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤትን እንዲሁም የፌደራል ፍትህና ህግ ኢኒስቲትዩትን የሚጎበኙ ይሆናል፡፡

Previous Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተጠናቀቀ
Next Article የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን መሰረት አድርጎ በሚቋቋም ልዩ ችሎት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲካሄድ የቆየው የምክክር መድረክ ተጠናቋል
Print
97