Wednesday, August 14, 2024 / Categories: News የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ልዑክ ቡድን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የልምድ ልውውጥ አደረገ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ፣ ምክትል ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሙሉዓለም እንዲሁም የስራ ሃላፊዎችን ያካተተ ልዑክ ቡድን በቀን 06/11/2016 ዓ.ም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡ በቆይታቸውም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሪፎርም፣ የቴክኖሎጂ፣ የሰው ሀብትና የዳኝነት ዘርፍ ላይ ሰፊ ገለጻ የተደረገላቸው ሲሆን ከመልካም ተሞክሮዎቹ ጎን ለጎን ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱ እርምጃዎች ላይም ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ለአዲስ ተሿሚዎች መልካም የሥራ ዘመን በመመኘትና በቀጣይም የማህበረሰቡን የፍትሕ ፍላጎት ያማከሉ ሥራዎች እንዲሠሩ በማሳሰብ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ክቡር ፕሬዝደንቱ አክለውም በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ልማት ላይ የዋሉት ቴክኖሎጂዎች ህዝብ እንዲገለገልበት ስራ ላይ የዋሉ እስከሆኑ ድረስ በየክልሎች ወርዶ አገልግሎት ላይ እንዲውል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ድጋፍ በማድረግ በአጠቃላይ ፍርድ ቤቶች ላይ የህዝብ አመኔታ እንዲኖር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አለምንተ አግደው በበኩላቸው በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጅማሮዎች መኖራቸውን ገልጸው ልምድ ልውውጡ እነዚህን ጅማሮዎችን በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠልና የተሻሉ አሰራሮችንና ተሞክሮዎችን በማካተት ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል። ለዚህም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን አመስግነዋል። የልዑክ ቡድኑ አባላት በቆይታቸው የፍርድ ቤቱን በቴክኖሎጂ የተደራጁ የችሎት አዳራሾችን (ስማርት ኮርት ሩም)ን፣ የዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ ዳታ ሴንተር እና ሌሎች የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴዎች ጎብኝተዋል። Previous Article ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችና የስራ ሃላፊዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ፕሮግራም ተጠናቀቀ Next Article ፍርድ ቤቱ የህጻናት ቀለብ አወሳሰን መምሪያና የዳኞች ለህጻናት ተስማሚ ፍትህ የስልጠና ማንዋልን አስመረቀ Print 300