የአሜሪካ ኤምባሲ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስማርት ኮርት ሩም የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን አበረከተ
/ Categories: News

የአሜሪካ ኤምባሲ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስማርት ኮርት ሩም የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን አበረከተ

የአሜሪካ ኤምባሲ በአምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ አማካይነት በቀን 13/12/2016 ዓ.ም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት በ300,000 ዶላር የሚገመት ድጋፍ ይህም ለ13 ስማርት ኮርት ሩም የሚያገለግሉ ኮምፒውተሮች፣ ካሜራዎች፣ መቅረጫ ቁሶች እና ስማርት ቲቪዎችን ያካተተ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን አበርክቷል፡፡

የቴክኖሎጂ መሳሪያዎቹን ያበረከቱት አምባሰደር ኤርቪን ማሲንጋ በመክፈቻ ንግግራቸው ፍርድ ቤቱ የጀመረውን የለውጥ ጉዞ አድንቀው የአሜሪካ መንግስት እነዚህን ውጥኖች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን እንዲሁም ቀልጣፋ የፍርድ ቤት ሥርዓቶች ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር፣ ተጠያቂነትን፣ ግልፅነትን እና ፍትሃዊነትን ለማጎልበት ወሳኝ በመሆናቸው የፍርድ ቤት አመራሮች የፍርድ ቤት ማዘመን ላይ በትኩረት መስራታቸውን በመቀጠል በመላ ሀገሪቱ የስማርት ፍርድ ቤት አገልግሎቶች እንዲስፋፋ ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው የስማርት ኮርት አገልግሎት አሰጣጥ ሥራ ላይ መዋሉ የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እና ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸው ለዚህ የሚሆኑ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ከአሜሪካ ኤምባሲ መበርከታቸው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከማጠናከር ባሻገር የፍርድ ቤታቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በዲጂታል ዘዴ የታገዘ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

ክቡር ፕሬዝደንቱ አክለውም ድምጽን ወደጽሑፍ ለመቀየር፣ የቪዲዮ ኮንፍረንስ ለማካሔድ፣ የኢፋይሊንግ አገልግሎት ለመስጠትና ተከራካሪ ወገኖች ካሉበት ቦታ ሆነው ክርክራቸውን ለማካሔድ የሚያስችሉ በመሆኑ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው ብለዋል፡፡

በእለቱም የአሜሪካ ኤምባሲ አምባደሩና ልዑክ ቡድኑ በፍርድ ቤቱ የሚገኙትን የስማርት ኮርት ሩሞችንና የዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ ዳታ ሴንተርን የጎበኙ ሲሆን በቀጣይ በጋራ ስለሚሰሩባቸው የትብብር መስኮች ላይም ውይይት አድርገዋል፡፡

Previous Article ፍርድ ቤቱ የህጻናት ቀለብ አወሳሰን መምሪያና የዳኞች ለህጻናት ተስማሚ ፍትህ የስልጠና ማንዋልን አስመረቀ
Next Article የወንጀል ፍትህ ስርአት ለማሻሻል በሚያስችሉ የትብብር መስኮች ላይ ከስዊድን ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ጋር ውይይት ተደረገ
Print
1302