Friday, September 20, 2024 / Categories: News የአሜሪካ ኤምባሲ የዓለም አቀፍ ናርኮቲክስ እና የሕግ ተፈጻሚነት ቢሮ ልኡክ ከፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ጋር የአጋርነት ውይይት አካሄደ በአሜሪካ ኤምባሲ የዓለም አቀፍ ናርኮቲክስ እና የሕግ ተፈጻሚነት ቢሮ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር/ Bureau of International Narcotics and Law Enforcement (INL)/ የሌና ዘሩ ፣ በምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ የዓለም አቀፍ የሕግ ዕድገት ልማት /International Law Development Organization(IDLO) East and Horn Africa/ ተወካይ አዳም ሽረው ጀማ ፣ በIDLO ዋና ቢሮ የፕሮግራም ልማት ኦፊሰር ስቴፋኖ ኮንሲግሎ እና በአሜሪካ ኤምባሲ INL ፕሮግራም ረዳት ትርሲት አጎናፍር ያካተተ ልኡክ ከፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ጋር በቀን 09/01/2016 ዓ.ም የአጋርነት ውይይት አካሄዷል፡፡ በቆይታቸውም የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ተቋማዊና ሙያዊ አቅም በዘላቂነት መገንባት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ፣ ሀገር አቀፍ የተከላካይ ጠበቆች አቅም ግንባታ አስፈላጊነት ፣ በሰብዓዊ መብቶች አከባበር እና ፍትሃዊ ሙግት ስርዓት በማጠናከር ሕብረተሰቡ በፍርድ ቤት እና በፍትህ ተቋማት ላይ ያለዉ አመኔታ እንዲያድግ ለማድረግ ተከላካይ ጠበቆች አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ስላለዉ ጠቀሜታ ፣ በስነምግባር የታነፀና በሙያዊ ብቃቱ ምስጉን ተከላካይ ጠበቃ ማብቃት በተለይ አቅም በማጣት ለፍትህ መጓደል ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ስላለዉ ፋይዳ ፣ መሰረታዊና ስነስርዓታዊ ፍትህ ተግባራት ተከላካይ ጠበቃ ማዕከል ማድረግ ስላለዉ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ፣ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር እና ውጤታማ እና ቀልጣፋ ማድረግ ስለሚቻልባቸው እና ሌሎች በቀጣይ ስለሚሰራባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ ውይይት አድርገዋል፡፡ በተለይም ጠንካራ የተከላካይ ጠበቆች ስልጠና ካሪኩለም አዘጋጅቶ ዘላቂ ሙያዊ የአቅም ግንባታ ተግባራት ማከናወን ፣ ተቋማዊ አቅም በዘላቂነት ማጠናከር የሚያስችሉ ድጋፎች እና የክልል ተከላካይ ጠበቆች ቢሮ ጋር በመቀናጀት ሀገራዊ የፍትህ ስርዓቱን በዘላቂነት ማገዝ እንዲቻል ችግሮቹ ላይ የጋራ መርሐግብር አዘጋጅቶ መምከርና መተግበር አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል። በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት አቅም ለሌላቸዉ እና በራሳቸዉ ጠበቃ መቅጠር የማይችሉትን በመወከል በሁሉም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከመጀመሪያ ደረጃ ክርክር እስከ ሰበር ችሎት የተከላካይ ጥብቅና አገልግሎት በተለይም የሕግ ምክር አገልግሎት ፣ የሕግ ክርክር ሰነዶች ዝግጅት እና ተገልጋዮችን በችሎት በመወከል የሕግ ክርክር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። Previous Article የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ልዑክ ቡድን በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመገኘት የልምድ ልውውጥ አካሄደ Next Article የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ልዑክ ቡድን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የልምድ ልውውጥ አደረገ፡፡ Print 361