የአዋጅ መሻሻልን ተከትሎ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የችሎት አደረጃጀትና የዳኞች አሰያየም ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት ለተጨማሪ ግዓብት ለውይይት ቀረበ
/ Categories: News

የአዋጅ መሻሻልን ተከትሎ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የችሎት አደረጃጀትና የዳኞች አሰያየም ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት ለተጨማሪ ግዓብት ለውይይት ቀረበ

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 እና ሌሎች ተከታታይ የአዋጁ ማሻሻያዎችን በመሻር በጥር ወር 2013 ዓ.ም  በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጸደቀው አዲስ አዋጅ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐ ብሔር ስረ-ነገር ሥልጣን ላይ ለውጥ ማድረጉን ተከትሎ በፌዴራል መጀመሪያ ድረጃ ፍርድ ቤት ሊኖር ስለሚችል የችሎት አደረጃጀት እና የዳኞች አሰያየምን ለማመላከት የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ውጤት ሚያዚያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ለፍ/ቤቱ አስተባባሪ ዳኞች፤ ዳኞች፣ ለሬጂስትራሮችና ለልዩ ልዩ የስራ ክፍል ኃላፊዎች ለአስተያየት ቀረበ፡፡

የተሸሻለው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ እስከ 10 ሚሊየን ብር የሚደርሱ የፍትሐበሔር ጉዳዮች በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲታዩ ስልጠን የሰጠ ሲሆን የጥናቱ አስፈላጊነት ከፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ወደ ፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የወረዱ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ለማስተናገድ የሚያስችል አደረጃጀትና የዳኞች አሰያየም ስርዓት ለመዘርጋት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሚወጣው መመሪያ እንደግብአት እዲያገለግል መሆኑን አጥኚዎቹ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱን ውጤት ይፋ ያደረው የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የህግ ጥናትና ድጋፍ ክፍል የጥናቱ ዋና ዓላማ ፍርድ ቤቱ የተደራጀ፣ ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉትን ችሎቶች ቡጉዳይ ዓይነት ለማደራጅት እና እንደየችሎቱ ዓይነት የሚሰየሙ ዳኞችን ቁጥር ብዛት ለመወሰን የሚረዳ በጥናት ላይ የተመሰረተ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ መሆኑን ገልጿል፡፡ 

የዳሰሳ ጥናቱ ከፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ወደፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የወረዱ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን የኮንስትራክሽን፣ የንግድ፣ የባንክ እና ኢንሹራንስ፣ የውል እና ከውል ውጪ በማለት የከፈላቸው ሲሆን እነዚህን ጉዳዮች የሚያዩ ችሎቶች የት ይደራጁ? በየችሎቶቹ የሚሰየሙ ዳኞች ቁጥርስ ስንት ይሁን? ለሚሉ ጥያቄዎች ምክንያታዊ መልስ አመላክቷል፡፡

በዚሁ መሰረት ጥናቱ አንድን ጉዳይ በአንድ ዳኛ ወይም በሶስት ዳኞች ለማየት የጉዳዩ ውስብስብነት እና መዝገቡ የያዘው የገንዘብ መጠን ከግምት እንዲገባ ሀሳብ ያቀረበ ሲሆን በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚነሱ የህግ ክርክሮች በመደበኛው የሕግ ዕውቀት ብቻ ሊመለሱ የማይችሉ በመሆናቸው የሚቀርቡት ማስረጃዎች ሙያዊ ዕውቀትንና ክህሎትን የሚጠይቁ ስለሆነ በችሎቶቹ ላይ ሊሰየሙ የሚገባቸው ዳኞች ቁጥር ከአንድ በላይ ሊሆን እንደሚገባ በማሳያነት ቀርቧል፡፡

በሌላ በኩል የንግድ ችሎት በአንድ ዳኛ ተሰይሞ ያለውን የመዝገብ ፍሰት ከግምት በማስገባት በውስን ምድብ ችሎቶች በቂ ችሎት ተቋቁመው ተገልጋዮች እንዲስተናገዱ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

የባንክና ኢንሹራንስ ጉዳይ በአንድ ዳኛ ተሰይሞ አሁን ባለው የችሎት አወቃቀር ከልደታና ቂርቆስ ምድብ ችሎት በተጨማሪ በሌሎች ችሎቶች እንዲታይ ሀሳብ ቀርቦበታል፡፡

በተመሳሳይ ውል እና ከውል ውጪ ኃላፊነትን (Extra-Contractual Liability) በተመለከተ የሚቀርቡ ጉዳዮች በርካታ በመሆናቸው ከሌሎች ችሎቶች ጋር በልዩ ልዩ ፍትሐብሔር ችሎቶች ስር ከሚታዩ ይልቅ ራሱን በቻለ ችሎት፤ በአንድ ዳኛ ቢስተናገዱ ጥሩ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችልና እነዚህ ጉዳዮች በቦታ የሚገደቡ ባለመሆናቸው በሁሉም ምድቦች ችሎቶች ቢቋቋሙ መልካም እንደሚሆን በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

ችሎቶችን በአንድና በሶስት ዳኞች የማስቻል ሁኔታ ያለው ጥቅምና ጉዳይት በጥናቱ የተመላከተ ሲሆን ለውሳኔ ጥራትና የፍርድ ቤቱን የህዝብ አመኔታን ለማሳደግ ችሎቶች በሶስት ዳኞች ቢሰየሙ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡  በአንጻሩ በፍ/ቤቱ ካሉት ዳኞች ቁጥር እና በይግባኝ ወደ ከፍተኛ የሚቀርቡ ጉዳዮች እንደዚሁ በሶስትና ከዛ በላይ በሆኑ ዳኞች እንዲታዩ የሚያስገድድ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

የቀረበውን የጥናት ውጤት ተከትሎ ከተሳታፊዎቹ በርካታ አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን የችሎት አደረጃጀቱ እና የዳኞች አሰያየም በዋናነት ከአገልግሎት ተደራሽነት፤ ቅልጥፍ፤ ጥራት እና የህዝብ አመኔታ ከማግኘት አንጻር ውጤታማነትን የሚያሳድግ እንዲሆን አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ በጥናት ላይ የተመሰረተ ምክረ ሃሳብ እንዲቀርብ ማድረጉን አድንቀዋል፡፡ 

በተመሳሳይ የውሳኔ ጥራትና የህዝብ አመኔታ ከዳኞች ቁጥር መብዛት ጋር ብቻ በቀጥታ የሚያያዝ ሳይሆን ከዳኞች ሙያዊ ብቃት እና ስነምግባር ጋር የተያያዘ በመሆኑ መዛግብት የሚይዙት የገንዘብ መጠን በችሎት ለሚሰየሙ ዳኞች ቁጥር መነሻና ለጉዳዩ ውስብስብነት መለኪያ ሊሆን እንደማይችል በዳኞች አስተያየት ቀርቧል፡፡ 

በተጨማሪም ችሎቶች በጥናቱ በቀረቡት ጉዳዮች ዓይነት መለየታቸው በተሳታፊ ዳኞች ቅቡልነት ያገኘ ሲሆን ችሎቶች ተደራሽ ሊሆኑ በሚችበት ምድብ ችሎቶች እንዲደራጁ ተጨማሪ ጥናት የሚያስፈልገው መሆኑን አንስተዋል፡፡  በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቶች የሚደረገው የዳኞች አሰያየም በከፍተኛ ፍ/ቤት ላይ የራሱ ተጽእኖ ሊኖረው ስለሚችል ተናቦ መስራት አንደሚያስፈልግ ዳኞች በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም በፍርድ ቤቱ ተደራጅተው በስራ ላይ ስላሉት የአፈጻጸም ችሎቶች የወደፊት እጣ ፈንታ ዳኞች አስተያየት እንዲሰጡበት ለቀረበላቸው ጥያቄ ዳኞች በሰጡት አስተያየት፤ የአፈጻጸም ጉዳዮች ውሳኔውን በሰጠው ችሎት/ዳኛ/ መታየት አለባቸው ብለዋል፡፡  ለዚህም ውሳኔውን በደንብ የሚያውቀውና የሚፈጸምበትን ሁኔታ በተሻለ የሚረዳው ውሳኔውን የሰጠው ዳኛ ነው፤ ግልጽነት ለጎደላቸው ውሳኔዎች አፈጻጸም ችሎቱ ማብራሪያ ሲጠይቅና መልስ ለማግኘት የሚወስደው ጊዜ የፍርድ አፈጻጸሙ እዲጓተት ያደርጋል፤ ውሳኔውን የሰጠው ችሎት የሚያስፈጽመው ራሱ ከሆነ የውሳኔ ጥራት እንዲጨምር ያደርጋል እና የመሳሰሉት ሃሳቦች በምክንያትነት ቀርበዋል፡፡  

ውይይቱን የመሩት የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ፕሬዝደንትና ም/ፕሬዝደንቶች በጥናቱ ላይ ያላቸውን ጥቅል አስተያየት ከሰጡ በኋላ በተሻሻለው አዋጅ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የችሎት አደረጃጀትን የሚወስን መመሪያ የማውጣት ስልጣን የተሰጠው መሆኑን በመግለጽ ይህ የጥናት ውጤት የቀረቡ አስተያየቶችን በማካተት ለመመሪያው ዝግጅት ግብአት አንዲሆን ይደረጋል ብለዋል፡፡

ለተጨማሪ ግብዓት የቀረበው ይህ የጥናት ውጤት ለጠበቆች፣ ለህግ ባለሙያዎችና እንዲሁም ውስን ለሚሆኑ ተገማች የፍርድ ቤቱ ባለጉዳዮች ቀርቦ ተጨማሪ ግብዓት የሚሰበሰብበት መሆኑ ተገልጿል፡፡    

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article የፌዴራል ፍ/ቤቶች ከፍተኛ አመራር እንዲያጸድቅ በቀረቡለት ሁለት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ተወያየ
Next Article የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
Print
456