Friday, August 2, 2024 / Categories: News የአውሮፓ ሕብረት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሽከርካሪዎች ድጋፍ አደረገ የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደርን ለመደገፍ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የተለያዩ የድጋፎች ማዕቀፎችን የያዘ ፕሮጀክት ተቀርፆ በትግባራ ላይ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው እለት ማለትም ሐምሌ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ዘጠኝ (9) ተሽከርካሪዎችን ለፍርድ ቤቱ አስረክቧል፡፡ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተገኝተው ለመስክ ሥራ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎችን ለፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ያስረከቡት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ክቡር አቶ ሮናልድ ኮቢያ ናቸው፡፡ በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ባደረጉት ንግግር የአውሮፓ ሕብረት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሪፎርም ላይ የሚያደርገው ድጋፍ በዳኝነት ስርዓት መሻሻል ላይ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን በማውሳት ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ክቡር ሮናልድ ኮቢያ በበኩላቸው በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር አሁን በአውሮፓ ሕብረት ለፍርድ ቤቱ የተደረገው የተሽከርካሪ ድጋፍ ከታቀደው አንፃር አነስተኛ መሆኑን ገልጸው የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ባለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ የፍትሕ ዘርፉን ለመደገፍና ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ እና የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ለመደገፍም ዝግጁነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የርክክብ ሥነሥርዓት ከተከናወነ በኋላ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ ያስገነባውንና የዳኝነት አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ በታገዘ ሁኔታ ለመስጠት የሚያስችለውን ስማርት ኮርት ሩም (Smart Court Room) ጉብኝት ተደርጓል፡፡ Previous Article የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬደዋ ምድብ ችሎት የቢሮ እድሳት የምርቃት ስነ-ስርዓት ተካሄደ Next Article The European Union handed over vehicles to the Federal Supreme Court of Ethiopia. Print 2073