Monday, April 24, 2023 / Categories: News የአውሮፓ ሕብረት ለፍርድ ቤቱ በሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ለሚከናወኑ ሥራዎች አፈጻጸም ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተመለከተ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለተለዩ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥራዎች ማስፈጸሚያ የአውሮፓ ሕብረት የመደበው የገንዘብ ድጋፍ ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል የፍርድ ቤቱ አመራሮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ገለጹ፡፡ክብርት ፕሬዚደንትዋ ይህን የገለጹት የአውሮፓ ሕብረት ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥራዎች ማስፈጸሚያ ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ለሶስት ዓመታት የመደበው ድጋፍ በአግባቡ ጥቅም ላይ ስለሚውልበት ሁኔታ ሚያዚያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም በቢሾፍቱ ሐይቅ ሪዞርት ሆቴል በተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ላይ ለሚከናወን ሪፎርም የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2020 ያደረገው ስምምነት አካል የሆነና በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ሥራ ላይ የሚውል 2,000,000 (ሁለት ሚሊዮን) ዩሮ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመደበ መሆኑም ታውቋል፡፡የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን ያዘጋጀው በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ እርዳታ ቴክኒካዊ ድጋፍ ቡድን (Technical Assistance Unit) ሲሆን በመድረኩ ላይ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተውጣጡ 16 ያህል አመራሮች፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች እና ቡድን መሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ዓላማ በገንዘብ ድጋፉ አማካኝነት እንዲከናወኑ የተለዩ የፍ/ቤቱን የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ተግባራት በመፈጸምና በማስፈጸም ረገድ ሚና ያላቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች በፕሮጀክቱ እንዲከናወኑ በተለዩ ሥራዎች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና በውይይቱ ላይ ከተጠቀሱት ዝርዝር ተግባራት መካከል በኃላፊነት እንዲያከናውኗቸው የሚጠበቁ ሥራዎችን ተፈጻሚ ለማድረግ ራሳቸውን ከወዲሁ እንዲያዘጋጁ ለማስቻል ነው፡፡የመድረኩ ተሳታፊዎች ከመድረኩ ያገኙትን ግንዛቤ መሠረት በማድረግ በገንዘብ ድጋፉ እንዲከናወኑ የተለዩ ተግባራትን በቀጣይ የሥራ ክፍላቸው ዕቅድ አካል አድርገው ለአፈጻጸም እንዲዘጋጁና ለተግባራዊነቱም በባለቤትነት መንፈስ እና በቅንጅት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም በፍ/ቤቱ አመራሮች መልዕክት ተላልፏል፡፡የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ላይ ለሚከናወን ሪፎርም የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና በዩኒቨርሲቲዎች ለሚከናወን የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የገንዘብ፣ የቴክኒክ እና የምክር ድጋፍ በማድረግ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ Previous Article አጣሪ ጉባዔው በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ Next Article “ሙስናና ብልሹ አሠራርን መከላከልና መልካም ሥነምግባርን ማስፈን” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሥልጠና ለፍርድ ቤቱ የአስተዳደር ዘርፍ ሠራተኞች ተሰጠ Print 2608